Fana: At a Speed of Life!

አምራች ኢንተርፕራይዞች በተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አምራች ኢንተርፕራይዞች በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን ማምረት ላይ እንዲሰማሩ በምርምር የታገዘ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡
 
የኢንተርፕራይዙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ እንደገለጹት÷ አምራች ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ ነው፡፡
 
በዚህም ባለፉት ስድስተ ወራት 1 ሺህ 647 አዳዲስ አምራች ኢተርፕራይዞች ኢንዲቋቋሙና 6 ሺህ 819 ነባር ኢንተርፕራይዞች እንዲጠናከሩ በማድረግ ለ40 ሺህ 667 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አንስተዋል፡፡
 
በሌላ በኩል 399 ባለ ሃብቶች አስፈላጊውን ግንዛቤ በመፍጠር እና ሁኔታዎችን በማመቻቸት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ይዘው ወደ አመራች ዘርፉ እንዲገቡ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
 
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
 
በመርሐ ግብሩ 572 ስራ አቁመው የነበሩ ጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
 
በተለይም ንቅናቄው ኢንተርፕራይዞች በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ያላቸው ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል ነው ያሉት፡፡
 
ይሁን እንጂ አምራች ኢተርፕራይዞች በተኪ ምርቶች ላይ ለመሰማራት የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የክህሎት፣ የገበያ ትስስር፣ የመስሪያ ቦታና ሌሎች ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡
 
ችግሮቹን ለመቅረፍም ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከክልል ቢሮ አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም አምራች ኢንተርፕራይዞች በተኪ ምርቶች ላይ እንዲሰማሩ የዘርፉ አዋጭነትና አስፈላጊነት፣ የስራ እድል ፈጠራ አንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ በምርምርና ጥናት የታገዘ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.