Fana: At a Speed of Life!

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እና ህወሓት የከባድ መሣሪያዎችን መረካከብ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ እና በኬንያ በተደረሰዉ ሥምምነት መሠረት በትናንትናዉ ዕለት በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት አመራሮች መካከል የመጀመሪያ ዙር የከባድ መሣሪያ ርክክብ ተደርጓል፡፡

ርክክቡ ከመቀሌ ከተማ 36 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው “አጉላ ካምፕ” የተከናወነ ሲሆን÷ በርክክቡ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ታዛቢዎችም ተገኝተዋል።

በቀጠናው የተሠማራው የኢፌዴሪ ሠራዊት አመራር ሌተናል ኮሎኔል አለሜ ታደለ ÷ በመንግስትና በህዋሓት አመራሮች መካከል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የተለያዩ ዓይነት ከባድ መሣሪያዎችን መረከባቸውን ገልፀዋል፡፡

ህወሓት ለመከላከያ ሠራዊታችን ያስረከባቸው የመሳሪያ ዓይነቶችም ብረት ለበስ ታንኮች ፣ የተለያዩ ሚሊ ሜትር መድፎች፣ ሮኬቶች፣ ዙዎች፣ ሞርተሮች እና ፐምፐን ያጠቃለለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የርክክብ ሥነ-ሥርዓቱን ለመታዘብ የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ አረካካቢ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል ነው የተባለው፡፡

ከኅብረቱ አረካካቢዎች መካከል ብርጋዴር ብርጋዴር ጄኔራል አድዋ ልቡካን ፒተር በሁለቱም ወገኖች በኩል እየተደረገ ያለው የከባድ መሣሪያ ርክክብ የተጀመረውን የሠላም ጉዞ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰላምን የማስፈን ተግባር ዓለምን የሚስደንቅ ስለሆነ ለመላው ሕዝብና ስምምነቱን ተግባራዊ እያደረጉ ላሉ አካላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ ማለታቸውን ከ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.