አዲስ ወግ ‘ሕዝባችን ዐቅማችን’ በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 ዓ.ም የመጀመሪያው የአዲስ ወግ ውይይት “ሕዝባችን ዐቅማችን” በሚል ርዕስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኘላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ፣ የሥነ-ሕዝብ ባለሙያው ኘሮፌሰር ንጋቱ ገዳ እና ዶ/ር የሽጥላ ወንድሜነህ የመወያያ ሐሳብ አቅራቢዎች መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅኅፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
በውይይቱ ላይ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ፥ “የሕዝብ ቁጥር አቅም መሆን እንዲችል የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ዘርፎች በቅንጅት መሥራት አለባቸው” ብለዋል፡፡
የፖሊሲ ማጣጣም አሰራር ተዘጋጅቶ የማናበብ ስራ መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት፡፡
የሥነ-ሕዝብ ባለሙያው ፕሮፌሰር ንጋቱ ገዳ በበኩላቸው ፥ የሕዝብ ቁጥር መጨመር በከተሞች አካባቢ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮችን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስ የአሰራር ሥርዓቶችን ለመፍጠር ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።
ዶ/ር የሺጥላ ወንድሜነህ በበኩላቸው ፥ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ የጸጥታ ስጋቶች ላይ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
የጸጥታ ሥጋቶችን ለመቀነስ የሠላም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና የሲቪክ ባሕልን በማሳደግ በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡