Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንደገለጹት÷ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የመከላከያ ሠራዊት ከህወሓት ታጣቂዎች ከባድ የጦር መሣሪያዎችን መረከብ ጀምሯል፡፡

ይህም የሰላም ስምምነቱ መሬት መንካት መጀመሩን የሚያመለክት እንደሆነ ጠቁመው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነቱ ዳር እንዲደርስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ያለ ምንም መስተጓጎል በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

እንዲሁም መንግሥት የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ መደበኛ አገልግሎቶችን ሥራ እንዲጀምሩ አድርጓል ብለዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሕገወጥ የታጣቂዎች ቡድን አባላትም የተፈጠረውን የሰላም ጥሪ በመቀባል ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ ከነትጥቃቸው ለፀጥታ ኃይሎች እጅ እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ሕብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ከሰላማዊ ሁኔታዎች ሁሉም እኩል ተጠቃሚና አትራፊ መሆኑን በአጽንኦት የገለጹት ዶክተር ለገሰ÷ የመላው ሕዝባችንን ችግሮችና ጥያቄዎች መቅረፍ የምንችለው አወንታዊና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ስንችል ነው ብለዋል።

ይህ እውን እንዲሆንም የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.