Fana: At a Speed of Life!

የሞባይል ስልክ በጦር መሣሪያ አስፈራርተው ወስደዋል በሚል የተከሰሱ የፖሊስ አባላት የምስክር አሰማም ሂደት ለጊዜው ተቋረጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሌሊት የግለሰቦችን ሞባይል በጦር መሣሪያ አስፈራርተው ወስደዋል ተብለው በከባድ የውንብድና ወንጀል የተከሰሱ ሦስት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ላይ የምስክር አሰማም ሂደት ለጊዜው እንዲቋረጥ ታዘዘ።

የምስክር አሰማም ሂደቱን ለጊዜው እንዲቋረጥ ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ÷ 1ኛ ኮንስታብል ሳሙኤል ጌቱ፣ 2ኛ ኮንስታብል ኢያሱ ጫሉ እና የፖሊስ አባል የሆነው አሽከርካሪ አንተነህ በቀለ ናቸው፡፡

የቦሌ ምድብ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው በተከሳሾቹ÷ የካቲት 16 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ 9:00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ መብራት ኃይል ፋና ገበያ ማዕከል አካባቢ ድርጊቱ መፈጸሙ ተጠቁሟል፡፡

1ኛ ተከሳሽ ክላሽ መሣሪያ በመያዝ፣ 2ኛ ተከሳሽ የእንጨት ዱላ በመያዝ እና 3ኛ ተከሳሽ ደግሞ የፖሊስ መኪና በማሽከርከር በሰዓቱ በገበያ ማዕከሉ የሚያልፉ አራት የግል ተበዳዮችን በማስቆም÷ መሬት ላይ እንዲንበረከኩ በማዘዝ ከግል ተበዳዮቹ ኪስ በመፈተሽ ሁለት 11 ሺህ 500 ብር የሚገመት የእጅ ሞባይል ስልክ በመውሰድ በ3ኛ ተከሳሽ የፖሊስ መኪና መሰወራቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ክትትል ተደርጎባቸው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ÷ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1 ሀ እና አንቀጽ 671/2 ላይ የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ለማወቅ ተችሏል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ፍርድ ቤቱ የዋስ መብታቸውን እንዲያከብር ባቀረቡት ጥያቄ መነሻ÷ እያንዳንዳቸው 13 ሺህ ብር አስይዘው ከስር እንዲፈቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ከስር የተፈቱ ቢሆንም ከዛ በኋላ በነበሩ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች የሕግ ግዴታቸውን አክብረው ሳይቀርቡ ቀርተዋል ነው የተባለው።

ፍርድ ቤቱም የፖሊስ አባላቱ በዋስ ያስያዙት ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን አዟል።

በተጨማሪም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በፖሊስ መጥሪያ እንዲደርሳቸው እና እንዲቀርቡ የታዘዘ ቢሆንም÷በተደጋጋሚ ቀጠሮ ምስክሮች ተሟልተው ሳይቀርቡ እንደቀሩ ተነስቷል።

ፖሊስም ምስክሮቹን በአድራሻቸው ሊያገኛቸው እንዳልቻለ መልስ ሰጥቷል።

በዚህ ምክንያት መነሻ ፍርድ ቤቱ፥ ምስክሮች ተገኝተው እስኪቀርቡ ለጊዜው የምስክር አሰማም ሂደቱ እንዲቋረጥ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.