Fana: At a Speed of Life!

የቻይና አፍሪካ ትብብር በእኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ው ፔንግን ተክተው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከአንድ ወር ቢፊት የተሾሙት ችን ጋንግ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የመጀመሪያቸውን የአፍሪካ ጉብኝት እያካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያን የመጀመሪያ መዳረሻቸው አድርገዋል።

በትናንትናው እለት አዲስ አበባ የገቡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን እና የቻይናን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል።

በዛሬው እለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ጋር በአህጉሪቱ እና በአገራቸው መካከል ያለውን ሁሉ አቀፍ ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ጥልቅ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፥ በጤና፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በምግብ ዋስትና መስኮች በመደጋገፍ ለመስራት የሚያግዝ ስምምነት ፈጽመዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በቻይና መንግስት ድጋፍ የተገነባውን እና የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታው የተጠናቀቀውን የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የቻይና እና የአፍሪካ ሁሉ አቀፍ ትብብር በእኩልነት፣ በወዳጅነት እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው።

የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሲራ ሲገባ በአፍሪካ ህብረት እንደሚተዳደር እና ተቋሙን ለታለመለት አላማ ማዋል የራሳቸው የአፍሪካውያን ጉዳይ መሆኑን እንዲሁም በዚህ ረገድ መንግስታቸው መንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንደማይኖረው አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት አገራት ለነዋሪዎቻቸው የተሻለች አህጉር እውን ለማድረግ እያደረገው ላለው ጥረት ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ፥ የመንገድ እና የባቡር መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ጤና፣ ግብርና፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ሰላም፣ ጸጥታ እና ምግብ ዋስትና የአገራቸው እና የአህጉሪቱ ዋነኛ የትብብር መስኮች እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ የሾመችው የቀጠናው አገራት ልማትን፣ ሰላም እና ጸጥታን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ ካላት ቁርጠኝነት የተነሳ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የኢትዮ ቻይና የባቡር መንገድ፣ የሞምባሳ የፍጥነት መንገድ እና የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል በቤልት ኤንድ ሮድ መርሃግብር መሰረት ቻይና ለአህጉሪቱ ልማት እያደረገችው ያለውን ተሳትፎ የሚያሳዩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ባለፉት 13 ዓመታት ቻይና የአፍሪካ ዋነኛ የንግድ አጋር ነች ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ በ2015 ዓ.ም የአገሪቱ እና የአህጉሪቱ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ከ260 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱን አስረድተዋል።

ቻይና ከአፍሪካ የምታስገባቸው ምርቶች መጠን ለማሳድግ ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል።

አፍሪካን ሰላም እና ልማት የተረጋገጠባት አህጉር ለማድረግ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እያደረጉት ያለውን ጥረት ማገዟን እንደምትቀጥል እና እንደ ሽብርተኝነት የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለማስቆም የሚደረገውን ትግል መደገፏን እንደምትቀጥልም ጨምረው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው፥ የማዕከሉን ግንባታ ቻይና ለአፍሪካ እያደረገችው ያለው ያላሰለሰ ድጋፍ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ጥልቅ ውይይትም የአፍሪካን እና የቻይናን ትብብር በሰላም እና በደህንነት፣ በጤና እና በምግብ ዋስትና ዘርፎች ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.