Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮች 10 ቀናት በተወሰኑ ሥፍራዎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ አሥር ቀናት ሰሜን ምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ በጥቂት ሥፍራዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የዓየር ሁኔታ ትንበያ መረጃዎች አመላከቱ፡፡

በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የዓየር ጠባይ አመዝኖ እንደሚቆይ እና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የደመና ሽፋን ሊኖር እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃ አመላክቷል፡፡

እንዲሁም በሰሜን ምሥራቅ፣ በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ በጥቂት ሥፍራዎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ተብሏል።

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት÷ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ የአፋር ዞን 2 እና4፣ የመካከለኛውና ምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮጉድሩ፣ የቤንች ማጂ ዞን እንዲሁም የሸካ እና ከፋ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡

የተቀሩት የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ደረቅ ሆነው ይቆያሉ ነው የተባለው::

በሌላ በኩል በአብዛኛው የሀገሪቱ ተፋሰስ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ የዓየር ጠባይ እንደሚስተዋል እና ከበልግ ወቅት መቃረብ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የበልግ እርጥበት ተጠቃሚ ተፋሰሶች ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ይጠበቃል፡፡

የዓየር ሁኔታ አዝማሚያው በግብርና ሥራ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ አንኳያም÷ አንዳንድ የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች መጠነኛ እና ቀጣይነት ያለው እርጥበት ሊያገኙ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ይህም የተሰበሰቡ ሰብሎችን ለመውቃት፣ በተዘጋጀላቸው ሥፍራ ለማከማቸት እና ወደ ገበያ ለማውጣት የሚያስችል በመሆኑ÷ በድኅረ ሰብል ስብሰባ ላይ የምርት ብክነት እንዳይኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ መክሯል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.