Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ፣ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የነዳጅ አምራች ተቋማት ከመንግስት ጋር እየመከሩ ነው – የማዕድን ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የሩሲያ፣ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ነዳጅ አምራች ተቋማት ከመንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ዛሬ በቀረበው የማዕድን ሚኒስቴር የ6 ወር የማዕድን ዘርፍ አፈጻጸም ሪፖርት እንደተመላከተው÷ ባለፉት 6 ወራት 1 ሺህ 910 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የወርቅ ምርት ተመርቷል፡፡

ለገበያ የቀረበው አብዛኛው የወርቅ ምርት በኩባንያዎች መሆኑ እና በባህላዊ አምራቾች የሚቀርበው የወርቅ ምርት መቀነስ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

ለገበያ የሚቀርበው የወርቅ ምርት እንዳያድግ የኮንትሮባንድ ንግድ ፈተና መሆኑእና በተለይም በባህላዊ መንገድ የሚመረተው የወርቅ ምርት ሕገወጥ ግብይት እንደሚታይበት ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም÷ ከክልሎች፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሰላምና ጸጥታ አካላት እንዲሁም ከፖሊስ ዐቃቤ ሕግ ግብረ ኃይል በማዋቀር እየተሠራ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በተጨማሪም ወርቅ በሚመረትባቸው ክልሎች በሚገኙ የወርቅ አዘዋዋሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴና የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

የማዕድን ዘርፉ የሚመራበትን መንገድ ከመቀየር ባለፈ ሕገወጥ ግብይቱን ለመከላከል አዲስ የማዕድን አዋጅ ተዘጋጅቶ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ነውየተባለው፡፡

ባለፉት ሥድስት ወራት 25 የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 22 የምርመራ ፣ ሦስቱ ደግሞ የማዕድን ምርት ፈቃዶች መሆናቸው በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ የማዕድን ኢንቨስትመንት ፍላጎት እየጨመረ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በነዳጅ ሀብቷ ዓለምአቀፍ ማረጋገጫ ካገኘች ወዲህ በዓለም ታዋቂ የሆኑ የነዳጅ ኩባንያዎች በንግግር ሂደት ላይ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

በአሁኑ ወቅትም የሩሲያ፣ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ነዳጅ አምራች ተቋማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በንግግር ሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው በሪፖርቱ የተመላከተው፡፡

ከነዳጅ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የፖታሽ ሀብት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች ወደ ሥራ እየገቡ ነው ተብሏል፡፡

የብረት ምርትን በተመለከተ ሀብቱ ያለባቸው አምስት ክላስተሮች የተለዩ ሲሆን፥ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የቁፋሮ ሥራ እየተጀመረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጸጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.