Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ አይቆምም – ኢንጂነር ታከለ ኡማ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ እንደማይቆም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አስታወቁ።

ኢንጂነር ታከለ በከተማዋ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን ላይ በከተማዋ የታክሲ አገልግሎትን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴ እንደማይቆም አስታውቀዋል።

ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ ታክሲዎች ትርፍ እንዳይጭኑ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር ታከለ፥ የከተማ አውቶብሶች በወንበር ልክ እንዲሁም ፈጣን ባቡር ተሳፋሪዎችን በግማሽ በመጫን አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ባለፈው ሳምንት የተደረገው የፀረ ተዋህስያን ኬሚካል ርጭት በተከታታይ እንደሚደረግ ጠቁመው፥ አስተዳደሩ ከአዲስ አባበ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ወደ ማምረት እየገባ መሆኑንም አስረድተዋል።

አሁን ላይም በሸማች ማህበራት አማካኝነት ከ200 ሺህ በላይ የእጅ ንጽህና መጠበቂያዎችን የማድረስ ስራ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም ለህብረተሰቡ የተለያዩ መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን በማህበራቱ በኩል የማቅረብ ስራ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

የህብረተሰቡን ጥግግት ለማስቀረትም ሰፋፊ የገበያ ስፍራዎች ወደ ሜዳማ አካባቢዎች እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልም በመዲናዋ ከ30 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰማራታቸውን ጠቁመው፥ የተለያዩ ድጋፎችን የማሰባሰብ ስራ በተደራጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ገንዘብና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጨምሮ፥ ከግለሰቦች ሆቴሎችና የመኖሪያ ቤቶች አስተዳደሩ ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት በድጋፍ መበርከታቸውን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ድጋፎቹን ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የማድረስ ስራ ይሰራልም ነው ያሉት።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 1 ሺህ 300 የንግድ ቤቶች መታሸጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.