Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ የተሽከርካሪ የብድር ውል ማስያዣ ሰነድ በማቅረብ የማታለል ተግባር ፈጽመዋል የተባሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የተሽከርካሪ የብድር ውል ማስያዣ ሰነድ በማቅረብ በተፈጸመ የማታለል ተግባር በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ላይ ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የተባሉ 5 ተከሳሶች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ በግል ስራ የሚተዳደሩት 1ኛ ተከሳሽ ሱራፌል በቀለ እና ባለቤታቸው 2ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ራኬብ መንግስቱ ፣ 3ኛ ተከሳሽ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ወረዳ 12 የደንበኞች አገልግሎት ባለሙያ የነበረው ግርማ ጊታ ፣ 4ኛ ተከሳሽ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ወረዳ 12 ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ አያሌው እና 5ኛ ተከሳሽ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሞተረኛ (መልክተኛ) የነበሩ ይድነቃቸው ዙማ ናቸው።

አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች ከአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ባለስልጣን የተሽከርካሪ ባለቤትነት በስማቸው ያልተመዘገበ በሌላ ድርጅትና ግለሰብ ስም የተመዘገቡ ሀሰተኛ የተሽከርካሪ የብድር ዋስትና ውልና ማስያዥያ በማቅረብ ከነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ/ም እስከ ታኅሣሥ 13 ቀን 2014 ዓ/ም ድረስ ባሉት ቀናቶች በቀሪ ተከሳሾች ተባባሪነት ተቋሙን በማታለል 1ኛ ተከሳሽ 10 ሚሊየን ብር መበደሩ ተገልጿል፡፡

2ኛ ተከሳሽ ደግሞ 6 ሚሊየን ከተቋሙ ብድር መውሰዳቸውን ፍርድ ቤቱ ማረጋገጡን ገልጿል።

ብድሩ ከተሰጠ በኋላ የቁጠባ ተቋሙ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የወሰዱትን ብድር አለመክፈላቸውን ተከትሎ በመያዥያ ያስያዙትን ተሽከርካሪ ሸጦ እዳውን ለማስመለስ ሲንቀሳቀስ የተሽከርካሪ ዋስትናዎቹ ሀሰተኛ ሆነው በመገኘታቸው በተቋሙ ላይ 1ኛ ተከሳሽ 9 ሚሊየን 777 ሺህ 074 ብር ከ90 ሳንቲም ጉዳት የደረሰ መሆኑንና በ2ኛ ተከሳሽ ደግሞ 5 ሚሊየን 208 ሺህ 430 ብር ከ70 ሳንቲም ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በዓቃቤ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

በተጨማሪም ችሎቱ 4ኛ ተከሳሽ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ወረዳ 12 ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ አያሌው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ማሟላት የሚገባቸውን እንዲያሟሉም ሆነ ብድሩ እንዲሰጣቸው ከዋናው ቢሮ ሳይፈቀድ ፎርማሊቲዎችን እንዲያካሂዱ በማድረግ የብድር ውል፣ የተሽከርካሪ ዋስትና ውል፣ የህይወት መድህን ውል፣ በቼክ ዋስትና ውል እንዲሁም የአንድነትና የነጠላ ኃላፊነት የተሽከርካሪ ዋስትና ውል በታኅሣሥ 23 ቀን 2014 ዓ/ም የሰጠ መሆኑ በዓቃቤ ህግ ማስረጃ ማረጋገጡን ፍ/ቤቱ አስታውቋል።

በዚህም ከ4ኛ ውጪ የሚገኙ ተከሳሾችን በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) እና ሀሰተኛ ሰነድ ማቅረብ ከባድ አታላይነት ወንጀል ድንጋጌ በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 142 መሰረት በሙሉ ድምጽ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

4ኛ ተከሳሽን ግን በወ/መ/ስ/ሕ/ቁጥር 113/2 መሰረት የተከሰሰበትን ስልጣንን አለአግባብ መጠቀም የሚለውን ድንጋጌ በመለወጥ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13/1/ሐ ስር ተከሳሹ በአንድ ዳኛ የሀሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምጽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቷል።

አንድ ዳኛ 4ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው የዓቃቤ ህግ ማስረጃ ወንጀሉን መፈጸሙን በተገቢው መንገድ የሚያስረዳ አይደለም ሲሉ በነጻ ሊሰናበት ይገባል የሚል የሀሳብ ልዩነት አቅርበዋል።

እንደአጠቃላይ ችሎቱ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መሰረት የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥር 24 እና ጥር 25 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.