Fana: At a Speed of Life!

ፒዮንግያንግ የኒውክሌር መርሐ- ግብሯን የማታቆም ከሆነ የኒውክሌር መሣሪያ ለመታጠቅ እንደምትገደድ ሴኡል ገለፀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሐ- ግብሯን የማታቆም ከሆነ የኒውክሌር መሣሪያ ለመታጠቅ እንደምትገደድ ደቡብ ኮሪያ ገለፀች፡፡

ከፒዮንግያንግ ጋር ያለው ውጥረት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ሴኡል ዘመናዊ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ልትታጠቅ ትችላለች ሲሉ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ-ዮል ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ወር ፒዮንግያንግን አግላይ እና አፋኝ ሲሉ የጠሩትን አጋርነት በማውገዝ ሀገራቸው አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳዬል እንደምታመርት መናገራቸውን ተከትሎ ነው፡፡

የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጠብ ጫሪነት እየበረታ የሚመጣ ከሆነ ደቡብ ኮሪያም በሁሉም ዓይነት የጦር መሣሪያ ራሷን ልታደራጅ አሊያም የራሷ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት ታደርጋለች ሲሉ ዩን መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ሁኔታው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ብዙ ጊዜ አይፈጅብንም ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በእኛ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ጊዜ ሳይፈጅ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ሊኖረን ይችላል ሲሉ አክለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.