Fana: At a Speed of Life!

ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ32 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት÷በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት ለሱዳንና ጅቡቲ ከቀረበ የኤልክትሪክ ኃይል ሽያጭ 32 ነጥብ 61 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ፡፡

ለሁለቱ ሀገራትም በጥቅሉ ከ580 ሚሊየን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤልክትሪክ ኃይል አቅርቦት መደረጉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የኤልክትሪክ ሃይል ለማቅረብ በቅርቡ በተደረገው ስምምነት መሰረት ኃይል ማቅረብ መጀመሯን ተናግረዋል፡፡

በ5 ወራት የተገኘው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ ያለው መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃቀም በተወሰነ መልኩ መቀነስ ማሳየቱ በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

የጎረቤት ሀገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከኢትዮጵያ ኃይል ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ ለሚቀርቡ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.