Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶችን በስነ ምግባር ለማነጽ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው – አቶ ሙስጠፌ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወጣቶች በስነ ምግባር እንዲታነጹና ባህላቸውን እንዲያጠናክሩ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ከክልሉ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና ማህበራት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ሙስጠፌ÷ የክልሉና የሀገሪቱን ቱባ ባህል በመጠበቅና በማስተዋወቅ እንዲሁም ሙዚቃና ባህል እንዲጎለብት የኪነጥበብ ባለሙያዎች የሚበረታታ ሥራ መስራታቸውን አንስተዋል፡፡

ወጣቶችን በስነ ምግባር በማነፅና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ በሙያቸው ግንዛቤ በማስጨበጥ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ሰላምን በማስፈንና የልማት ሥራዎችን ለማሳካት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ድርሻ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ህዝብን በማቀራረብ ረገድ እንደወትሮው ሁሉ በሙያቸው ህዝብን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉን ህዝብ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ አስተማሪና አዝናኝ ተውኔቶች በመስራት ለባህልና ኪነት እድገት ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ሰፊ ሥራ ይጠበቃል ፤ ለዚህም መሳካት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ  ያደርጋል ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ማህበራት በበኩላቸው÷የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና ለማህበራቱ የባህልና ሙዚቃ ቁሳቁሶች ድጋፍ እንዲሁም ስልጠናዎችን በመስጠት ዘርፉን ማጠናከር አለበት ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.