Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መበራከታቸው ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የቀለበት፣ አዳዲስ መንዶች እና ነባር የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ዳር መብራቶች አለመሥራታቸውን ተከትሎ ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎች መበራከታቸው ተገለጸ፡፡

አስተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ÷ በሥራችን ሁኔታና ባሕሪ ምክንያት አምሽተን የምንወጣ እና ለአዳር ሥራ ምሽት ላይ የምንገባ ሰዎች ጨለማን ተገን በማድረግ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ሥጋት ተፈጥሮብናል ብለዋል፡፡

የመንገድ ዳር መብራቶችን አገልግሎት አለመስጠት ተከትሎም ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ የስርቆትና የተለያዩ ወንጀሎች መበራከታቸውን ለመረዳት ተችሏል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በመዲናዋ በተለያዩ አካባበቢዎች ባደረገው ቅኝት÷ ከኃይሌ ጋርመንት ጓሮ፣ ከጓሮ አትሌቶች መንደር፣ ከአይ ሲ ቲ ማዕከል እስከ ቂሊንጦ፣ ከሃያት ዐደባባይ እስከ ቦሌ አራብሳ እና እንጦጦ በአዲሱ መንገድ የሚገኙ የመንገድ ዳር መብራቶች አገልግሎትየማይሰጡት መኖራቸውን ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም የወደቁ ፖሎች እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች የተቆረጡ ኬብሎች መኖራቸው ተስተውሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ዳር መብራቶች ጥገናና እድሳት የድንገተኛ አንስለሪ ሥራዎች ቡድን መሪ ዘውዱ ባይነህ በተጠቀሱ ቦታዎች የሚገኙ የአዳዲስና የቀለበት መንገድ ዳር መብራቶች አብዛኞቹ አገልግሎት እንደማይሰጡ አረጋግጠው÷ ለዚህም በትራንስፎርመርና በኬብል ላይ የሚፈጸምን ስርቆት በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ተቋማቸው የጥገናና እድሳት በማድረግ ወደ አገልግሎት ለማስገባት እንደሚሠራም ነው የጠቆሙት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌትሪክ አገልግሎት ቢሮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ሊኪሳ በበኩላቸው÷ በመብራት ትራንስፎርመሮችና ኬብሎች ላይ የሚፈጸመው የስርቆት ወንጀል መበራከቱን ተከትሎ የነባር መንገዶችና የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ዳር መብራቶች የመጥፋት ችግር አጋጥሟቸዋል ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚሰረቁት ዕቃዎችን በመተካት ጥገና በማድረግ መብራቶቹ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ ለመብራት እድሳትና ጥገና ሥራ 100ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደሚመደብ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሕብረተሰቡ መሰረተ ልማቱን የራሱ መሆኑን ተረድቶ የስርቆት ወንጀል ሲፈጸም ሊከላከልና ለፀጥታ አካላት ሊጠቁም እንደሚገባ ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.