Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረጊያው ጊዜ አሁን ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረጊያው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የደብረ ብርሃን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት፣ ንግድ እና ፋይናንስ ኤክስፖ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል፡፡

ኤክስፖውን በይፋ የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ÷ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረጊያው ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገሪቱ ከጦርነት ወጥታ ወደ ኢንቨስትመንት ፊቷን በማዞር ለምታደርገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የገጠሟትን አይነተ ብዙ ፈተናዎች  እየተወጣች የዜጎቿን ሁለንተናዊ እድገት ለማፅናት ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የስራችን ዋስትና የተፈጥሮ ሃብታችን እና የህዝባችን አቅም ነው ያሉት አቶ ደመቀ÷ የሀገራችን እምቅ የከርሰ ምድር እና የገፀምድር ሀብት ታላቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የህዝባችን ጥበብ፣ እውቀት፣ ጉልበት፣ ሀብት እና መስተጋብር ትልቅ አቅማችን ነው፤ እነዚህን ሀብቶች በዘመናዊ መንገድ ለማስተሳሰር ጠንክሮ መስራት ደግሞ የእድገታችንን ጉዞ አስተማማኝ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የሀብቶቻችንን አቅም አንጠፍጥፎ ለመጠቀም እና ለማስተሳሰር የሚረዱ መድረኮችን በተከታታይ ማሰናዳት ተገቢ ነው ያሉት አቶ ደመቀ÷ በኤክስፖው የታደሙ አምራቾች፣ ነጋዴዎች፣ የሥራ ፈጣሪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ተመራማሪዎች ለሀገራችን የሚተርፍ ትስስር እንደሚፈጥሩ እምነቴ የፀና ነውብለዋል ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥቂት በመሆናቸው መሬት የወሰዱ ኢንቨስተሮች በአፋጣኝ ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠይቀዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው እንዲስፋፋ የክልሉ መንግሥት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን እና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ኤክስፖው በክልሉ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ካሳሁን እምቢአለ ባደረጉት ንግግር÷ ኤክስፖውን ግዙፍ ለማድረግ እና በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ 10 ኤክስፖዎች አንዱ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

በኤክስፖው÷ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ባለሃብቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት ፣ ነጋዴዎችና አምራቾች ተሳታፊ ናቸው።

ኤክስፖው የተዘጋጀው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ሲሆን እስከ ጥር 14 ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

በፍቅርተ ከበደ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.