Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የምክር ቤቱ ውሳኔ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔውች አሳልፏል፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ለሁለተኛው ምዕራፍ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከዓለም ዐቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተደረገ 107,174,255.00 (መቶ ሰባት ሚሊዮን አንድ መቶ ሰባ አራት ሺ ሁለት መቶ አምሳ አምስት) የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት ላይ ነው፡፡ ብድሩም የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት እና የመሬት ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ገቢና አኗኗር ለማሻሻል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የሚደግፍ፤ ወለድ የማይታሰብበት እና በ40 ዓመታት ተከፍሎ የሚያልቅ መሆኑ ከአገሪቱ የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ምክር ቤቱ ስምምነቱን በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ ከየካቲት 2012 ጀምሮ ስራ ላይ በዋለው የኤክሳስ ታክስ አዋጅ ያስገኘውን ጠቀሜታ እንዲሁም የታዩትን ክፍተቶች በመገምገም በአንዳንድ ምርቶች ላይ የተጣለውን የማስከፈያ ምጣኔ ማስተካከል ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ የአዋጁ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱን ተግባርና ኃላፊነት ግልጽ ማድረግ፣ እያከናወነ ያለውን የምርምር ምህዳር በሌሎች የጤና ምርምር ስራዎች አስፍቶ እንዲሰራ ለማስቻል፣ ቅንጅትን የሚያጎለብት፣ ብክነትን የሚቀንስና ውጤታማነትን የሚያበረታታ አደረጃጀት እንዲኖረው የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ግብአቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

4. ምክር ቤቱ በመቀጠል የተወያየው የኢትዮጵያ የደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ቀደም ሲል ብሄራዊ የደም ባንክ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በማስፋት የደም ተዋፅኦዎችን፣ ሪኤጀንቶችን እና የደም ውሃ በአገር ውስጥ ማምረት እንዲሁም የቲሹ (ህብረ-ህዋስ) ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎትን የመደገፍ፣ የህብረ-ህዋስ ለጋሾችን የማስተባበር እና ተያያዥ ተግባራትን እንዲያከናውን የሚያስችል ስልጣን ያለው ተቋም በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ግብአቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

5. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም የቀረበው ረቂቅ ደንብ ነው፡፡ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን አስቀድሞ የመተንበይ፣ የመከላከል እና ምላሽ የመስጠት ውጤታማ ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤ የሀገሪቱ የጤና ላቦራቶሪ ዘርፍ ለህብረተሰብ ጤና ክብካቤ፣ ህክምና እንዲሁም ለስርዓተ ምግብ ምርምሮች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል የሚገባ በመሆኑ፤ የማህበረሰብ ጤና ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን አፈፃፀም በጥልቀት የሚከታተልና የሚገመግም ተቋም በማስፈለጉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ግብአቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

6. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣንን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የህክምና መሣሪያ፣ የባህላዊ መድኃኒት፣ የትምባሆ እና ተያያዥ ምርቶችን አመራረት፣ ዝውውር፣ አቅርቦት እና አጠቃቀምን በሚመለከት የቁጥጥር እና ክትትል ስርዓት መዘርጋት፣ የቁጥጥር ተግባሩን ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ ላቦራቶሪዎችን የማደራጀት፣ ህገ ወጥ ተግባራት ሲፈጸሙም ተገቢውን እርምጃ የሚወስድ እንደሁም ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች አመራረትና አጠቃቀም በአለም አቀፍ ስታንዳርዶች መሰረት መከናወናቸውን የሚያረጋግጥና የሚያስፈጽም ስልጣን እና አደረጃጀት ባለስልጣኑ እንዲኖረው የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ተወያይቶ ግብአቶችን በማከል በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

7. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው ከቱርክ ሪፐብሊክ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስታት ጋር በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ የመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ለማድረግ በተፈረሙ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ በወንጀል ጉዳይ የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ በመስጠት ረገድ ለሚደረገው የሁለትዮሽ ትብብር የሕግ ማዕቀፍን የሚፈጥሩ ከመሆኑም በላይ በተዋዋይ ሃገራት የህግ የበላይነት መረጋገጥ ፋይዳቸው የጎላ ነው፡፡

በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነቶቹም በተደራጁ፣ ድንበር ዘለል በሆኑ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ግዛቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ በሚከናወኑ የምርመራ፣ የክስና የፍርድ ሂደቶች መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲሁም የወንጀል ፍሬዎችን ዝውውር በመግታት ረገድ ፋይዳቸው የላቀ የትብብር የሕግ ማዕቀፎች በመሆናቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረቡት የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.