Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ከዲፕሎማቶች ጋር የሀገርን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማስፋፋት ያለመ ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ነባርና አዳዲስ ዲፕሎማቶች የሃገሪቱን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት በጋራ መስራት ላይ ያለመ ውይይት አደረጉ።

የመርሐ ግብሩ ዓላማ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲ እና የንግድ አቅጣጫን ለማመላከት በሚረዱ ሃሳቦች ላይ ውይይት ለማድረግ መሆኑን የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ኢ/ር መላኩ አዘዘው ተናግረዋል።

የውጭ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን በመሳብ ባሉን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የአምባሳደሮች ሚና ከፍ ያለ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ወቅታዊ የንግድ፣ ገበያ፣ ቴክኖሎጂና መሰል መረጃዎችን ተደራሽ እንድታደርጉልን እንዲሁም ከኢትዮጵያ በኩል የሚከናወኑ ንግድ ትርዒቶችን፣ ኮንፍረንሶችንና የገበያ ፍላጎቶችን፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን፣ የቱሪዝም መስህቦችን እንድታስተዋውቁልን እንፈልጋለን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታአምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ፥ ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር ወጥታ አሁን ላይ በተሻለ መንገድ ላይ ትገኛለች ፤ ስለዚህ ይህንን እድል ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ልንቀይር ይገባል ብለዋል።

አምባሳደሮች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ያነሱት አምባሳደሩ ፥ ይህ ደግሞ የታለመለት ማስታወቂያ ሊሆን ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት።

በረከት ተካልኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.