Fana: At a Speed of Life!

ለጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ እንግዶች አማራጭ የጉብኝት ፓኬጅ ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ እንግዶች አማራጭ የጉብኝ ፓኬጅ ማዘጋጀቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጥምቀት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም÷ በዋናነት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በጎንደር በልዩ ሁኔታ ስለሚከበር ጎብኚዎች እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ጥምቀትን በጎንደር ለረዥም ጊዜ ኢትዮጵያውያን፣ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መጥተው የሚያከብሩት በዓል ነው።

የጥምቀት በዓልን ለማክበር የሚመጡ እግዶችም የጥምቀት በዓልን ማክበር ብቻ ሳይሆን÷ በጎንደር አካባቢ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ መስኅቦችን መጎብኘት እንዲችሉ ልዩ ልዩ የጉብኝት ፓኬጅ ቀርጸናል ብለዋል።

አማራጭ የጉብኝት ፓኬጆቹ ለጥምቀት በዓል ከምናስተዋውቀው ሥራ ጋር እንዲቀርቡ በማድረግ አዲስ አበባን ጨምሮ÷ በደቡብ፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚጎበኙ ቦታዎችን ከጥምቀት በኋላ ወይም በፊት ማየት እንዲችሉ የቀረቡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ለጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን አምባሳደሮች ጥምቀትን በጎንደር በዓይናቸው አይተው እንዲያስተዋውቁ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡

ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ስለሺ በበዓሉ ላይ÷ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፣ የፓርላማ አባላት፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ባለቤቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና ሌሎች አካላት እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ ከመሆኑ አንፃር በሚከበርባቸው ቦታዎች ሁሉ ምዕመኑ እንዲሁም የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጭምር ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ የበዓሉ ታዳሚዎች በሰላም አክብረው እንዲመለሱ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኮቪድ-19 እና በግጭት ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደነበረበት ወይም ከዛ በላይ ማደግ እንዲችል አስተዋጽኦ የሚበረከትበት ጊዜ ስለሆነ ሁሉም ከቱሪዝም ማህበረሰቡ ጎን እንዲቆም ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የጥምቀት በዓል መንፈሳዊ ይዘቱ ዋና መሰረት ሆኖ ባህላዊ አልባሳት፣ ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ፣ የምግብና መጠጥ አቅርቦትና ሽያጭ የሚከናወንበት መሆኑንም አውስተዋል፡፡

ስለሆነም በዓሉ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ ስላለው ሁሉም ከከተራ ጀምሮ ለጥምቀት በዓል በድምቀት መከበር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ ስለሺ ግርማ ጠይቀዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.