Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ባህር ሃይል በደቡብ ቻይና ወታደራዊ  ልምምድ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና የባህር ሃይል በደቡብ ቻይና በሚገኘው ባህር የጦር ልምምድ ማድረጉ ተገለጸ፡፡

ቻይና የባህር ሃይል ልምምዷን የጀመረቸው የአሜሪካ ባህር ሃይል በዚሁ የደቡብ ቻይና ባህር አቅራቢያ የጦር  ልምምድ ማድረጉን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

በወታደራዊ ልምምዱ በቀጠናው አላስፈላጊትንኮሳ የሚፈጽሙ አውሮፕላኖችን ይከላከላሉ የተባሉ ጄ-15 ተዋጊ ጄቶች ሻንዶንግ ከተባለው ስፈራ በመነሳት አስፈላጊውን ስልጠና ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

የቻይና ባህር ሃይል ባደረገው ወታደራዊ ልምምድ በአየር እና በውሃ ውስጥ የመከላከል እና የማጥቃት ስልጠናዎችን በብቃት መውሰዱ ተመላክቷል፡፡

የአሜሪካ የባህር ሃይል ቀደም ሲል ኒሚትዝ በተበላው የባህር ሃይል ቡድን “የኢንዶ ፓስፊክ “ኦፕሬሽን አካል የሆነውን የጦር ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

ስትራቴጅካዊው የደቡብ ቻይና ባህር ይገባኛል የምትለው ቤጂንግ ÷ በአካባቢው በገነባቻቸው ሰው ሰራሽ ደሴቶች ላይ ወታደራዊ ማዕከሎችን መመስረቷ ነው የተገለጸው፡፡

ዋሽንግተን በበኩሏ÷ ቤጂንግ በደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ ያቀረበችውን የይገባኛል ጥያቄ ህጋዊ አይደለም፤በባህር አሰሳ ስም በየጊዜው የጦር መርከቦችን ወደ አካባቢው እየላከች ነው ስትል ከሳለች፡፡

ከቻይና እና አሜሪካ በተጨማሪ ታይዋን፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ፣ ብሩኒ እና ፊሊፒንስ በሃብት የበለጸገውን የደቡብ ቻይና ባህር የይገባኛል ጥያቄ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.