Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ ከበዓል አከባባር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደርግ እንደሚገባ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥምቀት በዓል አከባባር ጋር ተያይዞ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ሊደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ፡፡

አገልግሎቱ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን በመግለፅ ፥ ከበዓሉ አከባባር ጋር ተያይዞ የእምነቱ ተከታዮች ቦታዎችን ሲያስውቡ የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል፡፡

የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ የሚከበር የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ በተለይ በከተሞች የተለያዩ የማስዋብ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጿል፡፡

የማስዋብ ሥራው ከሚከናወንባቸው ግብዓቶች አንዱ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች መሆናቸውን በማንሳት ወጣቶች ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በምሰሶዎች ላይ በመውጣት የማድመቀያ ቁሳቁሶችን የመስቀል ሥራዎች ሲሰሩ እንደሚስተዋል ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህም በየዓመቱ ከኤሌክትሪክ ንክኪ ጋር በሚፈጠሩ አደጋዎች በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል ነውያለው፡፡

ስለሆነም ለአከባበሩ ድምቀት የአሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመጠቀም የሚደረጉ የማስዋብ ሥራዎች ለኤሌክትሪክ አደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊከናወን እንደሚገባውና ድንገተኛ የኤሌክትሪክ አደጋ ካጋጠመም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል በመደወል ወይም አካባቢው በሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳውቅ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.