Fana: At a Speed of Life!

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ መንስኤ፣ ምልክት እና መከላከያ መንገድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ኩላሊትን፣ የሽንት ፊኛን እና የላይኛውን እና የታችኛውን የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦዎች የሚያጠቃ የኢንፌክሽን አይነት ነው።

ብዙዎቹ ኢንፌክሽኖች የታችኛውን የሽንት ቧንቧ እና የሽንት ፊኛን የሚያጠቁ ሲሆን÷ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ኢንፌክሽኖች ከሽንት ፊኛ አልፈው ወደ ኩላሊት ከተሻገሩ አሳሳቢ የጤና እክል እንደሚስከትሉ የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የሚከሰተው ባክቴሪያ ወደ ሽንት ቧንቧ ገብቶ በሚራባበት ጊዜ ነው።

የሽንት ሥርዓት በተፈጥሮ ባክቴሪያዎችን እንዲያስወግድ የተሠራ ቢሆንም÷ አንዳንዴ ተፈጥሯዊው መከላከያ መንገድ አሠራሩን በማሸነፍ ባክቴሪያዎች ወደ ሰውነት ገብተው በሽታ ሊያመጡ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡

ሴቶች በተለይ ባላቸው የሰውነት አቀማመጥ ምክንያት በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት፣ በማህፀን ውስጥ በሚቀመጡ አንዳንድ የወሊድ መከላከያዎች እንዲሁም የሴቶች ማረጥ ጊዜ የበለጠ ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ተጋላጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

በተጨማሪም ጤናማ ያልሆነ የሽንት ቧንቧ ኖሯቸው የሚወለዱ ሕጻናት፣ የሽንት ቧንቧ መደፈን፣ በኩላሊት ጠጠር ምክንያት፣ የበሽታ መከላከያ ሥርዓት መጎዳት፣ በስኳር በሽታ ምክንያት፣ አርቴፊሻል የሽንት ቱቦ (ካቴተር) የሚጠቀሙ ሕመምተኞች፣ የሽንት ፊኛ፣ ፕሮስቴት ወይም የኩላሊት ቀዶ ጥገና ያደረጉ ሰዎች ለሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አንዳንድ ጊዜ ምልክት ላያሳይ ቢችልም በአብዛኛው ግን÷ በመጠን አነስተኛ ግን በተደጋጋሚ ሽንት መሽናት፣ ደመናማ የመሰለ የሽንት ቀለም፣ የሽንት ቀለም ወደ ቀይ፣ ሮዝ ወይም ጠቆር ያለ መልክ መቀየር፣ ከሽንት ጋር የደም ምልክት መታየት፣ ያልተለመደ ጠንከር ያለ የሽንት ሽታ፣ ማህፀን አካባቢ የሚሰማ የመጫን ሕመም (ለሴቶች) ወይም ወንዶች ብልታቸው አካባቢ እና የሽንት ፊኛ አካባቢ የሚሰማ ሕመም ከሚታዩ ምልክቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡

ቀጥለው የተዘረዘሩትን ነጥቦች በመተግበር የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን መከላከል ይቻላል፡፡

 በቂ ውኃ መጠጣት÷ ውኃ መጠጣት ሽንትን ይበርዛል እንዲሁም ቶሎ ቶሎ እንድንሸና በማድረግ ባክቴሪያው ኢንፌክሽን ሳያመጣ ከሽንት ቧንቧ እንዲወርድ ያደርጋል።

 ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ የሽንት ቧንቧ አካባቢን ማጽዳት እንዲሁም ውኃ በመጠጣት ባክቴሪያው እንዲወገድ ማድረግ

 የወሊድ መከላከያ መንገዶችን መቀየር ካስፈለገ ሐኪም ማማከር በተለይ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ሕመም ካለ፡፡

 በጊዜ ሐኪም ማማከር እና መድኃኒት ከታዘዘ በአግባቡ በመውሰድ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽንን መከላከል እንደሚቻል ከጥቁር አንበሳ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.