Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል – ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ ቆይቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል በመሆኑ በርካታ ሕዝብ ይሳተፋል ያሉት ምክትል ኮማንደሩ ÷ ፖሊስም ይህንን የሚመጥን ዝግጅት አድርጎ በርካታ የፖሊስ አባላት ማሰማራቱን ጠቁመዋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ጃን ሜዳን ጨምሮ ከ278 በላይ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወደ ጥምቀተ-ባሕሩ እንደሚጓዙ እና 78 የሚደርሱ የታቦታት ማደሪያ ስፍራዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
ስለሆነም ፖሊስ በእነዚህ ቦታዎችላይ በእግረኛ ፖሊስ እንዲሁም በውሻ እና ፈረስ የታገዘ የወንጀል መከላከል ስራ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፡፡
 
ከዚህ ባለፈም በፖሊስ መሪነት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ አጋዥ አካላት መረጃ የመስጠት፣ የመቀበል ፣ ጥበቃ የማድረግ እና የማስተባበር ስራ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል፡፡
 
ህብረተሰቡ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር የበዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ገጽታ ከሚያንጸባርቁ መልዕክቶች ውጪ ሌሎች አላስፈላጊ ቅስቀሳዎችን ማድረግ የተከለከለ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
 
በተጨማሪም በጽሑፍም ሆነ በሌላ መንገድ ግጭት የሚቀሰቅሱ እና ሌላውን ማህበረሰብ ሊያውኩ የሚችሉ ነገሮች መኖር እንደሌለባቸው ነው ያብራሩት፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት፣ ከበጎ ፈቃደኞች እና ሌሎች አጋዥ አካላት ጋር አስፈላጊውን ትብብት እንዲያደርጉ ተጠይቀዋል፡፡
 
ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞም ታቦታቱ በሚወጡባቸው መንገዶች አሽከርካሪች መኪና ይዘው ከመምጣት እንዲቆጠቡ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ አሳስበዋል፡፡
 
ማህበረሰቡ በበዓል አካባበር ሥነ-ስርዓቱ ላይ አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11 ወይም በ991 ነጻ የስልክ መስመር ለፖሊስ እንዲያሳውቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.