Fana: At a Speed of Life!

በጥምቀት በዓል የእሳትና ድንገተኛ አደጋ እንዳያጋጥም ጥንቃቄ እንዲደርግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጥምቀት በዓል የእሳትና ድንገተኛ አደጋ እንዳያጋጥም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ አደጋዎችን መነሻ በማድረግ እንደስጋት የተለዩና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ሁኔታዎች አሉ፡፡

በዚህም ታቦታቱ እና ምዕመኑ እንዲያርፉበት በሚል ድንኳን በሚጣልባቸው ቦታዎች በሚዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ በሚያጋጥም መዘናጋት እንዲሁም የኤሌክትሪክ መስመሮቹ ከሰው ቁመት በታች ሆኖው የሚዘረጉበት አጋጣሚ በመኖሩ ለአደጋ ያጋልጣሉ ብለዋል፡፡

መስመሮቹ በጨለማ የማይታዩ በመሆናቸውም በሰዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ አመላክተዋል፡፡

ከኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ጋር በተያያዘ ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲደረግ ከሃይማኖት አባቶችና በጎ ፈቃደኞች ጋር ውይይት መደረጉን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በጥምቀት ዕለት ምዕመናን ፀበል ለመረጨት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሚፈጠር መገፋፋት÷ አንዳንድ ወላጆች ሕጻናትን ይዘው ወደ ግፊያ ውስጥ ስለሚገቡ እንዲሁም የጤና ችግር ያለባቸው (የልብ ድካም፣ የአካል ጉዳት፣ አቅመ ደካሞች) ጉዳት ሊደርስባቸው ስለሚችል ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ሥነ ስርዓቱ ተጠናቆ ወይም ታቦታቱ ሲወጡና ሲገቡ በሚሔዱበት መንገድ የረገቡ የኤሌክትሪክ መስመሮች ካሉ ታቦታቱን ለማጀብና እንደጥላ የሚያገለግሉ ከብረት የሚሠሩ የሚገፉ ሠረገላዎች ምናልባት የረገቡ የኤሌክትሪክ መስመሮች ጋር በመነካካት አደጋ እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በጥንቃቄ ጉድለት ከሦስት ዓመታት በፊት የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል፡፡

ኮሚሽኑን ጨምሮ በሚመለከታቸው አካላት አደጋን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ዝግጅት እንደተጠበቀ ሆኖ÷ ባልተጠበቀ ሁኔታ አደጋ ቢከሰት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዘጠኙ ቅርንጫፎች ዝግጅት አድርገዋል ተብሏል፡፡

ህብረተሰቡ በዐደባባይ በሚከበሩ በዓላትም ሆነ በመኖሪያ ቤት አደጋ ከሚያስከትሉ ሁኔታዎች እራሱን እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አደጋ ቢያጋጥም ህብረተሰቡ በነጻ የስልክ መስመር 939 እንዲሁም 0111 55 5300 እንዲያሳውቅ ተጠይቋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.