Fana: At a Speed of Life!

ከ65 ሚሊየን ብር በላይ የይዞታ ካሳ ክፍያ በሚል ያለአግባብ በመውሰድ የተከሰሱት 16 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 65 ሚሊየን ብር በላይ የውሀ ፕሮጀክት ስራ የይዞታ ካሳ ክፍያ በሚል ያለአግባብ ወስደዋል ተብለው በከባድ ሙስና ወንጀል የተከሰሱት የወረዳ 6 ስራ አስፈጻሚ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጠ።

ቀሪ ሌሎች 5 ተከሳሾች ደግሞ በዓቃቤ ህግ የቀረበባቸው ማስረጃን እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ በቦሌ አራብሳ አካባቢ በውሃና ፍሳሽ ተቋም ለሚገነባው ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ስራ ይዞታ ከሌላቸው 21 ግለሰቦች ጋር በዝምድ እና በጥቅም በመተሳሰር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ተደርጎ ስም ዝርዝር በማስገባትና በይዞታ ባለቤትነት በሀሰት ለመዘገቡ ቤተሰብና የተለያዩ ግለሰቦች ውክልና በመውሰድ ይዞታ በማረጋገጥ ፣ የይዞታ ካሳ በማጽደቅና እንዲሁም ከህግ ውጪ ከ65 ሚሊየን ብር በላይ የይዞታ ካሳ ክፍያ ገንዘብ በተለያዩ መጠኖች በ2013 ዓ.ም መጨረሻ በተለያዩ ቀናቶች መውሰዳቸው ተጠቅሶ በየካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶ ነበር።

ተከሳሾች ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም 2 የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ ናቸው፡፡

ከእዚህ ከስ ከቀረበባቸው 21 ተከሳሾች ውስጥ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገረመው ይገዙን ጨምሮ 16 ተከሳሾች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተከሳሾች መሆናቸውን ተከትሎ ችሎቱ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው እና ፖሊስ በአድራሻቸው አላገኘኋቸው የሚል መልስ በመስጠቱ በመጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ በሌሉበት መዝገቡ እንዲቀጥል ብይን ተሰጥቶ ነበር።

ቀሪዎቹ ግን ማለትም የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች የሆኑት አቶ በቀለ ገረሱ፣ ጫላ አለሙ ፣ ተስፋዬ አለሙ እንዲሁም የክፍለ ከተማው የካሳ መረጃ አሰባሳቢ ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት ገዛኸኝ አንቦ እና አብርሐም አለነ ክስ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ክሱ ደርሷቸው ጉዳያቸውን ተከታትለዋል።

ዐቃቤ ህግ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ላይ ከስድስት በላይ ምስክሮችን እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ በተለያዩ ቀናቶች አሰምቷል፤ ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሯል።

በዚህም በከባድ ሙስና ወንጀል የተከሰሱት የወረዳ 6 ስራ አስፈጻሚ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 16 ተከሳሾች ላይ በዛሬው ቀጠሮ በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ቀሪ ሌሎች 5 ተከሳሾች የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች የሆኑት አቶ በቀለ ገረሱ ፣ ጫላ አለሙ፣ ተስፋዬ አለሙ እንዲሁም የክፍለ ከተማው የካሳ መረጃ አሰባሳቢ ባለሙያዎች ናቸው የተባሉት ገዛኸኝ አንቦ እና አብርሐም አለነ በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ምስክር እና የሰነድ ማስረጃ በክሱ ላይ የተጠቀሰው ወንጀል መፈጸሙ ተረጋግጧል ሲል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ የመከላከያ ማስረጃ እንዳላቸው በችሎቱ ዳኞች የተጠየቁ ሲሆን፥ መከላከያ ማስረጃ አለን ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፤ ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃን ለመጠባበቅ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.