Fana: At a Speed of Life!

የአውሮፓ ህብረት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት መንግሥት የፈጸማቸውን ተግባራት አደነቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት መንግሥት የፈጸማቸውን ተግባራት አደነቀ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር አኔት ዌበር ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አተገባበር ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ በኩል በርካታ ሥራዎችን እንደሰራ ገልፀዋል።

በዚህም መሠረታዊ አገልግሎቶች ዳግም እንዲጀምሩ መደረጋቸውን ፣የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲስፋፋ መደረጉን እና የተሀድሶ ኮሚሽን ተቋቁሞ ኮሚሽነር መሾሙንም አብራርተዋል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ያላትን አቋም ገልፀዋል፡፡

ሕብረቱ የፖለቲካ ግብን ያነገበው እና የሰብአዊ መብቶች ጉዳይን እንዲመረምር የተሰየመው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን የሥራ ዘመን ከመጪው የአውሮፓዊያኑ መጋቢት ወር በኋላ እንዳይራዘም ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ በግጭቱ ወቅት የተፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት በስምምነቱ መሠረት በሽግግር ፍትህ መፍትሄ እንዲያገኝ እየሰራች መሆኑን መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኔት ዌበር በበኩላቸው÷ በስምምነቱ መሠረት መንግሥት የፈጸማቸውን ተግባራት አድንቀው ሕብረቱ የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.