Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚሲዮን መሪዎች የመልሶ ማቋቋም ሂደት ላይ የላቀ ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የሚሲዮን መሪዎች አገሪቱ በምታከናውነው መልሶ ግንባታ እና የመልሶ ማቋቋም ስራ ላይ ያላቸው ሚና የላቀ በመሆኑ ይህን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዚዳንቷ ለነባርና አዳዲስ አምባሳደሮች በተዘጋጀው የእራት ግብዣ መርሃግብር ላይ ተገኝተው የሥራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን÷ በዚህም አገሪቱ ከገጠማት ፈተና ለመሻገር ወሳኝ የሰላም እድል ፈጥራ ወደ ተግባራዊ ስራ መግባቷን ገልፀዋል።

በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ችግሩ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍና የወደሙ ንብረቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት አምባሳደሮቹ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ፕሬዚዳንቷ መመሪያ ተሰጥተዋል ።

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር እና ዓለም አቀፍ ጫና በገጠማት ጊዜ አምባሳደሮች ያደረጉትን በጎ ተግባር ያደነቁ ሲሆን÷ ዲፕሎማቶቹ የተወጡት ሃላፊነትም የሚዘነጋ አይደለም ሲሉ ገልፀዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና አገራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ መንግስት የሚሰጣቸውን አቅጣጫ በመከተል ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.