Fana: At a Speed of Life!

ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሸሽ በማድረግ የተጠረጠሩ 6 የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ 6 ሚሊየን ዶላር በላይ በ26 ግለሰቦች እንዲሸሽ በማድረግ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ስድስት የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ ምትኩ አበባው፣ ግርማ ይባፋ፣ እንግዳ አቦ፣ ማቲዎስ ከታ፣ ቤተልዬም ንጉሴ፣ ሜላት መስፍን የተባሉ የጉምሩክ ኮሚሽን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርጫፍ ሰራተኞች ናቸው።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የምርመራ ስራ እያከናወኑ የሚገኙት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ እና የፍትህ ሚኒስቴር የምርመራ ዘርፍ ዐቃቤ ህግ ጋር በጋራ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ 6 ሚሊየን ዶላር ከውጭ ሀገር ያስገቡ የተመዘገቡ የ26 ግለሰቦች የገንዘብ መጠን በመሰረዝ እና በመቀነስ አስተካክለው የጉምሩክ ሲስተም ላይ የማስቀመጥ ተግባር መኖሩን ዐቃቤ ህግ ለችሎቱ አስረድቷል።

ለማሳያ በሲስተም ላይ አንድ ግለሰብ ከውጭ ይዞ የገባውን 300 ሺህ ዶላርን በመሰረዝ 3 ሺህ ዶላር ብቻ አድርጎ ቀንሶ በማስቀመጥ ደረጃ ተሳትፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የገለጸ ሲሆን÷ 130 ሺህ ዶላር ያስገባ ሌላ ግለሰብን የገንዘብ መጠን ሰርዞ 30 ሺህ ዶላር ብቻ እንዲሆን በማድረግ ተሳትፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ጠቅሷል።

በሌላ በኩል በአንድ ግለሰብ ከቤልጂዬም ገብቷል ተብሎ በጉሙሩክ ኮሚሽን በዕቃ ወጪ ዲክሌር በተደረገበት ቀን በተደረገ የማጣራት ስራ የገባው እቃ ሳይሆን የውጭ ሀገር ገንዘብ ሆኖ መገኘቱን አብራርቷል።

በተለይም ከጉዳዩ ጋር የሚገናኝ በጉሙሩክ ኮሚሽን ቢሮ ውስጥ የጠፋ ሰነድ በአንድ የጉሙሩክ ሰራተኛ መኖሪያ ቤት በብርበራ መገኘቱን ዐቃቢ ህግ ጠቅሷል።

በተደረገ የማጣራት ስራ ከውጭ ዶላር በማስገባት ገንዘቡን አሽሽተዋል የተባሉ 26 ግለሰቦች በስማቸው በተለያየ ቁጥሮች እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ ስምንት ፓስፖርቶችን አውጥተው ከኢምግሬሽን መገኘቱን ዐቃቤ ህግ አብራርቷል።

ግለሰቦቹ በርካታ የባንክ ሒሳብ እንዳላቸው ከብሔራዊ ባንክ ማስረጃ እንደሰበሰበ የገለጸ ሲሆን፤ ለወንጀሉ መፈጸም የሚያስረዱ 10 የባለሙያና ሌሎች ምስክሮችና እንዳሉት ለችሎቱ ገልጿል።

የተመዘገቡ 26 ግለሰቦች ከ6 ሚሊየን ዶላር በላይ ወደ ሀገር ውስጥ ካስገቡ በኋላ ጥቁር ገበያ ላይ ከሚሳተፉ አካላት ጋር በመመሳጠር ገንዘቡ እንዲሸሽ መደረጉን ገልጿል።

በዚህ መልኩ ሀገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታጣ ተደርጓል ሲል ዐቃቤህግ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው” የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው ”ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ ”ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ የሚፈጥሩት ተጽኖ አለ ወይ? ” ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ ” በዋስ ቢወጡ ሲስተም ስርዓቱን ስለሚያቁ የግለሰቦችን የውጭ ሀገር ገንዘብ ማስረጃ ሊሰርዙና ሊያጠፉብን ይችላሉ” ሲል ዐቃቤህግ ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሞ ተከራክሯል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከኢሚግሬሽንና ከብሔራዊ ባንክ የተሰበሰበ ማስረጃንና የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ ተመልክቷል።

ከወንጀል ድርጊቱ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ የመደረጉን አስፈላጊነት በማመን ለፖሊስ ተጨማሪ 14 ምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.