Fana: At a Speed of Life!

ምስጢረ ጥምቀት

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘመነ ኦሪት እንደሚከበረው በዓለ ዳስ የአደባባይ በዓል የሆነው “በዓለ ጥምቀት” ምስጢር ብዙ ነው፡፡

ወደ ወንዝ ሄዶ በመጠመቅ ከበሽታ መፈወስም የተለመደ መሆኑን በኢዮብ እና በሶርያዊው ንእማን ታሪክ ላይ ተሠንዶ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መነሻነት የዘመነ ኦሪቱ ጥምቀት ለመንጻት(ለመፈወስ) ነው ተብሎ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይወሰዳል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ኃላፊ መልአከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በኦሪትና በሐዲስ ኪዳን መካከል ወይንም በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን መካከል የጌታን መንገድ የጠረገው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው ይላሉ፡፡

“ቅዱስ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ያጠምቅ ነበር፤ የሚያጠምቀውም ፍሬን የሚያሰጥ የማዘጋጃ የሆነ የንሥሐ ጥምቀት ነበር” ሲሉም ያስረዳሉ።

ጥምቀት ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ይዞ ወደ ክርስትናው ዓለም ገብቶ በትርጉምና በምክንያትነት ሲለይ፥ ሂደቱ ግን ከዘመነ ኦሪት ተያይዞ የመጣ መሆኑን አባ ቃለ ጽድቅ ይናገራሉ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትና ዛሬ ምዕመኑ የሚጠመቀው ጥምቀት በውኃ ውስጥ በመዘፈቅ፣ ብቅ ጥልቅ በማለት ቢመሳሰሉም፥ በትርጉማቸው ግን የተለያዩ መሆናቸውን በአጽንኦት ይገልጻሉ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀው ለመንጻት፣ ለንስሃ እንዲሁም ምዕመናን ልጅነትን ለማግኘት እንደሚጠመቁት ለልጅነትም አይደለም ሲሉ ያስረዳሉ።

“ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው ትኅትናን ለማስተማር ነው፤ መምህረ ትኅትና ፣ በዓርያም በዙፋኑ የሚኖር ወልደ ዓብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወደ አገልጋዩ ቅዱስ ዮሐንስ መምጣቱ÷ ራሱን ዝቅ አድርጎ መቅረቡንና ትኅትናን ለማስተማር መሆኑን መገንዘብ ይገባልም” ነው የሚሉት።

“ቅዱስ ዮሐንስ ‘አንተ በእኔ ልትጠመቅ አይገባም፤ እኔ ነኝ ባንተ መጠመቅ የሚገባኝ’ ባለው ጊዜም÷ ‘ፍቀድልኝ ትንቢቶች መፈጸምና ምሳሌዎቹም መከናወን አለባቸው’ በማለት ምላሽ ሰጥቶታል፤ እሱ መፍቀድ የሚገባው አምላክ ፈቃድን ከአገልጋዩ መጠየቁ ትኅትናን ለማስተማር መሆኑን መረዳት ይገባል” በማለት ያስረዳሉ።

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ሌላው ምክንያት አርአያ ለመሆን ነው የሚሉት መልአከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለ ጽድቅ፥ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ሲመላለስ እንደ አምላክነቱ ለማዳን ፤ ሰው እንደ መሆኑም ለእኛ አርአያ በመሆን ነው ይላሉ።

አርአያ የሆነባቸው በርካታ ነገሮች መሆናቸውን ጠቁመው፥ “ጾም የማይገባው ለእኛ አርአያ ለመሆን መጾሙ፤ ጥምቀት የማይገባው ጥምቀታችንን ለመመስረት መጠመቁ፤ ጸሎት የማይገባው መቀበል እንጅ እሱ መጸለይ የማይመለከተው ስለኛ ለእኛ አርአያ ለመሆን መጸለዩ ለአብነት ያህል ይጠቀሳሉ” ሲሉ ያስረዳሉ።

“የእኛ ጥምቀትና የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የማይገናኝ ሲሆን፥ የእሱ ጥምቀት ለእኛ ጥምቀት መሠረት ሆኗል፡፡ እኛ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠምቀን ልጅነትን ከሥላሴ እናገኛለን፡፡ ሁለተኛ መወለድ የሚለውንም ልጅነት ከሥላሴ እናገኝና ሰማያዊ ዜግነትን እንቀዳጃለን፡፡ አዲስ ስምም እናገኛለን (የክርስትና ስም)” በማለት አስረድተዋል።

ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው በጥምቀት መሆኑን ገልጸው፥ አንድ ክርስቲያን ወደ ክርስትናው ህብረት መግባቱ የሚረጋገጠው በጥምቀት ነው ይላሉ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀበት ሦስተኛው ምክንያት “የሰው ልጆችን የዕዳ ደብዳቤ” ለመደምሰስ መሆኑ ተገልጿል፡፡

“የዕዳ ደብዳቤ ማለት የበደል ጽሑፍ ነው፤ የሰው ልጅ ወዶና ፈቅዶ ባፈረሰው የእግዚአብሔር ትዕዛዝ መሠረት የተቀበለው ከገነት መውጣት ከአባቱ ከእግዚአብሔር መለየት ነበር፡፡ በዚህም አገልጋይነቱ፣ ታዛዥነቱ፣ ለዲያብሎስ ሆኖ ነበር” ሲሉ ያብራራሉ፡፡

“ታሪክ እንደሚያስረዳን ‘አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ’ የሚል ጽሑፍ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል እንዳስቀመጠ አባቶቻችን በታሪክ ያስተምራሉ፤ ትውፊትም ያስረዳል” ሲሉ ዶክተር አባ ቃለ ጽድቅ ይናገራሉ፡፡

“ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል” ነው የሚሉት፡፡

“አራተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ምክንያት ‘እኔ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ሲወርድበት የምታየው የምታጠምቀው እሱ ነው’ አለኝ ብሎ ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ገለፀው÷ የኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ መገለጥ ነው። ከዚህ የተነሳ ዘመኑ ‘ዘመነ አስተርዮ ‘ የመገለጥ፣ የመታየት ዘመን ይባላል” ሲሉ ያብራራሉ፡፡

“መገለጥ የሚለው ደግሞ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የተገለጠበት፤ የታየበት ነው። ይህም እግዚአብሔር ወልድ እንደ አንድ የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በእርግብ አምሳል በእሱ ላይ ወርዶ ሲታይ እግዚአብሔር አብ ደግሞ በደመና ሆኖ ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው’ ብሎ ሲመሰክር ሦስትነቱን ገልጧል፤ በአንድ ድምፅ አንድነቱንም አሳይቷል” ይላሉ፡፡ ስለዚህ አንድነቱንና ሦስትነቱን በፈለገ ዮርዳኖስ እንዲገለጥ አድርጓል በማለት አስረድተዋል።

“ክርስቲያኖች በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ትኅትናን የምንማርበት፣ ስለ እኛ እኛን ሆኖ እራሱን ዝቅ አድርጎ እኛን ያስተማረውን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናስብበት ነው” በማለት መልአከ ሰላም ዶክተር አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ አስገንዝበዋል፡፡

ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ላይ ማለትም ከምሥጢረ ንስሥሐ ቀጥሎ የሚቀመጠው ምሥጢረ ጥምቀት፥ በኢየሱስ ክርስቶስ መጠመቅ ላይ መመሥረቱ፣ ምዕመኑ ልጅነት ያገኘበት እና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር መሆኑ ተገልጿል፡፡

“የክርስቶስ አካል ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን አካል ውስጥ ለመቆጠር የሚያስችለን ምሥጢረ ጥምቀት ነው፤ ስለዚህ ይህንን ሁሉ ያገኘንበት ‘ጥምቀት’ ታላቅ በዓል ነው” ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

“ኢየሱስ ክርስቶስ በአደባባይ የተገለጠበት በዓል ስለሆነ በአደባባይ እናከብራለን፤ ታቦታተ ሕጉን ይዘን እየዘመርን እግዚአብሔርን እያመሰገን በአደባባይ የምናከብረው በዓል ነው” ይላሉ፡፡

“ኢትዮጵያውያን ፣ ኦርቶዶክሳውያን በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠንን ፀጋ እያመሰገንን፣ ደስ እያለን፣ ያገኘንበትንም ልጅነት፣ የተማርንበትንም ትኅትና ያገኘነውን ፀጋ ሁሉ እያከበርን በዓሉን ልናከብር ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.