Fana: At a Speed of Life!

የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ የመፍትሔ አማራጭ ለመቋጨት መንግሥት የጀመራቸውን ጥረቶች አሁንም አጠናክሮ መቀጠሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር አብዛኞቹ አካባቢዎች ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ጋር በመተባበር ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የመሠረታዊ አገልግሎቶች በተለይም የጤና፣ ባንክ፣ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክና የንጹህ ውኃ አቅርቦቶችም አቅም በፈቀደ መጠን አገልግሎቶቹ ተቋርጦባቸው በነበሩ አካባቢዎች በከፍተኛ ጥገናና መልሶ ግንባታ ዳግም አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በመጀመሩም ተቋርጦ የነበረው የሕዝብ ለሕዝብና የማህበራዊ ግንኙነት ወደ መደበኛነት መመለሱን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በበርካታ አካባቢዎችም የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩን ጠቁመው ለአብነትም÷ በአክሱም፣ ዓድዋ፣ ሽረ አካባቢ እና በአላማጣ የሕዝቦችን ትስስር በሚያጠናክር መልኩ የየብስ ትራንስፖርት እንዲጀመር ተደርጓል ብለዋል፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እስከ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ባለው ወቅት ብቻ በመንግሥት በኩል 15 ሺህ 23 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ምግብ ነክ ቁሳቁስ፣ 113 ሺህ 952 ሊትር ነዳጅ እንዲሁም 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለሥራ ማስፈጸሚያ እና ለአገልግሎት ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

29 የተለያዩ አጋር አካላትን ባሳተፈ መልኩ ደግሞ÷ 149 ሺህ 496 ነጥብ 33 ሜትሪክ ቶን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የእርዳታ ቁሳቁስ፣ 1 ሺህ 562 ነጥብ 76 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት፣ ከ4 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ አልሚ ምግብ በሰሜኑ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ነው ገለጹት፡፡

በፕሪቶሪያው፣ በናይሮቢ አንድ እና ሁለት ስምምነት መሠረት አካባቢዎቹን ከውጥረትና ከግጭት ነጻ ለማድረግ እንዲሁም ሰላማዊ ሁኔታ በአካባቢው ለመፍጠር ሰፋፊ ሥራዎች በመንግሥት በኩል እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በህወሓት በኩልም ታጣቂዎቹን ወደ አንድ አካባቢ የማሰባሰብ ፣ ከባድ መሳሪያዎችን አሰባስቦ ለማስረከብ የሚደረግ ጥረት በአዎንታዊ መልኩ የሚታይ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

በትግራይ ያለው ህብረተሰብም ሁሉም ዓይነት መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ፣ ያልተገደቡ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ፣ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ፣ የንግድ ሥርዓት እንዲሳለጥ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ መደበኛ ሥራ እንዲገቡ ፍላጎት እንዳለ መንግሥት ይገነዘባል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡

እንደዚህ ዓይት ፍላጎቶች እንዲስተካከሉ መንግሥት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገም ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ይህ በአንድ ወገን ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ በሰላማዊ ስምምነቶቹ መሰረት በሁሉም ወገን በተመሳሳይ ፍጥነት መጠናከር አለበት ብሎ መንግስት እንደሚያምን አንስተዋል፡፡

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት በመንግስት በኩል በሰላም ስምምነቱ ከተቀመጡ የድርጊት ጊዜዎች ሦስት አራት እጥፍ እርምጃዎችን የተሻገረ ጥረቶችም እየተደረጉ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

ለዚህ አንዱ ማሳያ በትግራይ ክልል በመቀሌና ውቅሮ ከተሞች የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ለማስገባት የሚረዳና ስለ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ አጠቃላይ መረጃ ለማሰባሰብ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት የሚያካሂድ ቡድን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ተልኮ እንዲፈጽም ተደርጓልም ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ፥ የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት መሰረት በማድረግ በክልሉ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ፣ በቀላሉ ድጋፍና ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የሚገቡት የትኞቹ እንደሆኑ፣ የኢንዱስትሪዎቹ የጉዳት መጠን ታውቆ በፍጥነት ወደ ማምረት ለማስገባ የሚያስችል የመጀመሪያ ደረጃ ጥናትና ምልከታ ተደርጓል፡፡

በዚህ ላይ ተመስርቶም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም በጥናቶቹና በሪፖርቶቹ ላይ ውይይት ተደርጓልም ነው ያሉት፡፡

የጥናቶቹና የውይይቶቹ መሰረታዊ ዓላማ የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ይበልጥ ለማጎልበት እንዲቻል፣ በተለያዩ መንገዶች ጉዳት የደረሰባቸውን አምራች ኢንዱስትሪዎች በአስቸኳይ ፤ አንዳንዶቹም በፍጥነት ተጠግነው ወደ ተግባር እንዲገቡ ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ፣ ወደ መደበኛ አገልግሎት ከታሰበው ቀድሞ እንዲገቡ ለማድረግ ያለመ ነውም ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግሥትም እንዲህ ዓይነቶቹን ድርጊቶች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ተገልጿል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የታሰበለትን ግብና ዓላማ እንዲያሳካ የስምምነቱ አካል የሆነው አንዱ ወገን ስለሌላው ወገን አሉታዊ መረጃዎችን ከማሰራጨት መቆጠብ አለበት የሚለው ድንጋጌና መርህ በጥብቅ መከበር እንዳለበት መንግሥት ያምናል ብለዋል ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፡፡

በመንግሥትና መንግስት በሚጠቀምባቸው ሚዲያዎች ይህ መርህ እስካሁን ድረስ በጥብቅ የሚከበር ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ በመሆኑ ይህ ነው የሚባል ያጋጠመ ችግር የለም ነው ያሉት፡፡

በአንጻሩ በአንዳንድ የህወሓት አመራሮች ከስምምነት ያፈነገጠ አኳኋን፣ አሉታዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ሲተላለፉ እየተስተዋለ ይገኛል ፤ እነዚህም በፍጥነት መታረም ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ለአብነት ያህልም የአጎራባች የክልል የጸጥታ አካላትን ጨፍጫፊ አድርጎ የመግለጽና የሚኮንን መልዕክት አዘል ጉዳዮችን ማስተላለፍና በትግራይ ክልል ውስጥ በተፈጸሙ ወንጀሎች ህወሓት እንደሌለበትና ቡድኑን ንጹህ አድርጎ ማቅረብ እየተስተዋሉ ነውም ብለዋል፡፡

ይህም ከሰላም ስምምነቱ ጋር የሚጋጭና ስምምነቱን በሙሉ ልብ ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥላ እንዳያጠላ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል በመግለጫቸው፡፡

በዚህም ጉዳዩን ለሚመለከታቸው የህወሓት አመራሮች የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ በመንግስት በኩል የተገለጸላቸው በመሆኑ በቅርቡ እነዚህ ችግሮች ይስተካከላሉ ብለን እንጠብቃለንም ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.