Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ተጨማሪ አምስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ተጨማሪ አምስት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ባለፈው 24 ሰዓታት ውስጥ 59 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል ብሏል።

ሶስቱ ታማሚዎች ኢትዮጵያውያ ሲሆኑ፥አንዱ ኤርትራዊ እና አንዱ ደግሞ ሊቢያዊ ናቸውም ነው የተባለው።

በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው አምስቱ ግለሰቦች በአዲስ አበባ የሚገኙ መሆናቸው ነው የተነገረው ፡፡

አንደኛው ቫይረሱ የተገኘበት የ26 ዓመት ወጣት ከዱባይ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ ሁለተኛው የ60 አመት ግለሰብ ከኮንጎ የመጣ እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ ሶስተኛ የ45 አመት ግለሰብ ከካናዳ የመጣና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረ፣ አራተኛዋ የ27 አመት ወጣት ከእንግሊዝ የመጣች እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበረች እንዲሁም አምስተኛው የ30 አመት ወጣት እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዛሬውን ውጤት ጨምሮም እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 43 መድረሱን ነው ሚኒስቴሩ ያመለከተው።

በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆነው ህክምናቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር 37 ሲሆን፥ አንድ ሰው በጽኑ ህክምና ላይ ሲሆን አራት ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፤ ሁለቱ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.