Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ እየተስፋፋ ከመጣው በቴክኖሎጂ የታገዘ መጭበርበር ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ እየተስፋፋ ከመጣው በቴክኖሎጂ የታገዘ መጭበርበር እራሱን እንዲጠብቅ የፌደራል ፖሊስ እና የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አሳሰቡ፡፡

ሰሞኑን በቴክኖሎጂ በታገዘ መጭበርበር 122 ሺህ ብር የተወሰደባቸው ግለሰቦች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያቀረቡትን ጥቆማ መሰረት በማድረግ የፌዴራል ፖሊስ እና የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎትን ስለሁኔታው ማብራሪያ ጠይቀናል፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ጀይላን አብዲ በበኩላቸው፥ ህብረተሰቡ ባልተወዳደረበትና ባልተሳተፈበት ሁኔታ “ሽልማት (ስጦታ) ደርሷቹሃል፤ ስጦታችሁን ለመውሰድም የስጦታ ማስፈጸሚያ ገንዘብ ክፈሉ” ከሚሉ አጭበርባሪዎች እራሱን ሊጠብቅ ይገባል ይላሉ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ማጭበርበሮች ህብረተሰቡን ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ዕክሎች እየዳረጉት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከእነዚህ አጭበርባሪዎች ለመቆጠብ መፍትሔው በእጁ ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ክፍያ ከመፈጸሙ ወይም የትኛውንም ሂደት ከመጀመሩ በፊት ሊያስተውል እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ እንዳለ አሰፋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ቴክኖሎጂ ሠርካዊ እንቅስቃሴን የማቅለሉን ያህል በቀላሉ ጉዳት ለማድረስ ምቹ ስለሆነ በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡

ሰዎች ተጨማሪ ጊዜና ወጪ ሳያባክኑ ባለቡት ሆነው ገንዘብ ማንቀሳቀስና ጉዳያቸውን እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መሆኑ ቢታመንም፥ በአንጻሩ ከአጠቃቀም ጥንቃቄ ጉድለት ጋር በተያያዘ ሰዎች በቀላሉ የሚጭበረበሩበት ሁኔታ መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም ለተቋማቸው በርካታ ጥቆማዎች እንደሚደርሱ ነው ያረጋገጡት፡፡

አጭበርባሪዎቹ የደወሉለትን ግለሰብ ፍጹም በማይረዳበት ሁኔታ፣ ትኩረቱ ወደ ሌሎች ነገሮች እንዲሆን በማድረግ እና በማጣደፍ እነሱ ወደ ሚፈልጉት ዐውድ በማስገባት ነው የሚያጭበረብሩት ይላሉ፡፡

የተደወለላቸው ሰዎች የመጭበርበር ስሜት እንዳይሰማቸውም አጭበርባሪዎቹ እራሳቸው “ከዚህ በፊት የተለያዩ አካላት ካሰራጩት የማጭበርበሪያ ዘዴዎች ተጠንቀቁ፤ ይህ ትክክለኛ የጋራ ቢዝነስ ነው” በማለት ታማኝ ለመምሰል ጥረት እንደሚያደርጉም ከጥቆማዎች መረዳት ተችሏል፡፡

አጭበርባሪዎች ስጦታና ሽልማት እንደላኩ ሆነው ታማኝ ለመምሰል የታዋቂ ድርጅቶችን ስም እና ሎጎ በመጠቀም÷ ሕጋዊ የሚመስሉ ሀሰተኛ ሠነዶችን በመላክ ጭምር እንደሚያጭበረብሩ ተገልጿል፡፡

ከማጭበርበሪያ ስልቶች መካከል፥ ከሞባይል ባንኪንግ ጋር በተያያዘ (ስልክ በመደወል የአካውንታችሁን ደኅንነት የማረጋገጥ እና አንዳንድ መረጃዎች የማስተካከል ሥራ እየሠራን ስለሆነ መረጃ ይስጡን በሚል)፣ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም (ወዳጅነት በመመስረት ስጦታ እንደተላከ አድርገው ገንዘብ ተቀብሎ መሰወር) እንዲሁም ከመተግበሪያዎች፣ ድረ ገጾች እና ማስፈንጠሪያዎች ጋር በተያያዘ (ቀደም ሲል ፊት ለፊት ሰዎች በሚያመጡት አባላት ብዛት ጥቅም እንደሚያገኙ የሚሰጡ ስምሪቶች አሁን ማስፈንጠሪያዎችን በሚያጋሩት መጠን ልክ መሆን) የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ቴክኖሎጂው እየዘመነ ሲሄድ የማጭበርበሪያ ስልቱም ተለዋዋጭ በመሆኑ በጥቆማዎች መሠረት በሚደረግ ክትትል እንደተረጋገጠው፥ አጭበርባሪዎቹ ገንዘብ ከሰበሰቡና ጥቂት ሰዎች (በድለላ ሂደቱ የሚሳተፉ) ከተጠቀሙ በኋላ አድራሻ ቀይረው ይሰወራሉ፡፡

በአጠቃላይ የሰዎችን አዕምሮ በመስረቅ፣ አጓጊ ቁሶችን እና ገንዘብ በማሳየት በርካታ የማጭበርበር ሥራ እንደሚሠራ ደርሰንበታል ይላሉ፡፡

በመንግስት በኩል ቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሰተ በኋላም የሚደረገው ክትትል እንደተጠበቀ ሆኖ ህብረተሰቡ በቴክኖሎጂ ከታገዘ መጭበርበር እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊነት አጠራጣሪ ሁኔታዎች፣ ጥቆማዎች እና ተጨማሪ መረጃዎችን ሰብስቦ በመተንተን ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሔድበት ለፖሊስ ማስተላለፍ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በዚሁ መሰረት በሕግ የተያዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡ መሰል የማጭበርበር ሁኔታ ሲያጋጥመው በነጻ የስልክ መስመሮች 987 እና 816 ለፌዴራል ፖሊስ በተጨማሪም በ 991 ለአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም +251-11-812-8261 ለፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.