Fana: At a Speed of Life!

አንድ ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ምርመራ ሊያደርግ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የዓይን ምርመራ በማድረግ በዕይታ ላይ የሚያጋጥምን ዕክል መከላከል እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዓይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ እና የዓይን ሐኪም ዶክተር ሰሎሞን ቡሳ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ለዓይነ ስውርነት የሚዳርጉ መንስኤዎች በርካታ ናቸው፡፡

ለአብነትም÷ የሞራ ግርዶሽ፣ ግላኮማ፣ የትራኮማ በሽታ፣ አነጣጥሮ የማየት ችግር፣ የስኳር ሕመም (ዲያቢቲስ) እና ከመደበኛው የመወለጃ ጊዜ ቀድሞ መወለድ የሚሉት ዓይነ ስውርነት ከሚያስከትሉ መንስኤዎች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የሞራ ግርዶሽ በተፈጥሮ፣ በአደጋ እና በዕድሜ መግፋት ሊመጣ እንደሚችል ጠቁመው በኢትዮጵያ ከፍተኛው የዓይነ ስውርነት ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል ይላሉ፡፡

በአብዛኛው ህብረተሰቡ ወደ ሕክምና ተቋም የሚሔደው የዕይታ ችግር ሲደርስበት መሆኑን ገልጸው÷ ይህም የተሳሳተ ልማድ በመሆኑ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ምክንያቱም በዘር ሊተላለፉ የሚችሉ ከዓይን ጋር የተያያዙ ችግሮች እና የሕመም ምልክት ሳያሳዩ የዕይታ ብርሃንን የሚያጠፉ (ለምሳሌ ግላኮማ) ዓይነት ሕመሞች ስላሉ ነው ብለዋል፡፡

በተለይም ዕድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነው ሰው የዓይን ምርመራ ማድረግ ይጠበቅበታል ነው የሚሉት፡፡

ተማሪዎች ከጥቁር/ነጭ ሰሌዳ ላይ የሚጻፈውን ማየት ሲሳናቸው አነጣጥሮ የማየት ችግር ሊሆን እንደሚችል ተገንዝበው ሐኪም ማማከር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት አንድ ሰው ከሦስት ሜትር ጣት መቁጠር ካቃተው የዕይታ ችግር አለበት ተብሎ እንደሚፈረጅም አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.