Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ የምግብ ምርትን አስመልክቶ 2ኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ በዚህ ሣምንት በዳካር ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የምግብ ምርትን አስመልክቶ ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ይካሄዳል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች እና መንግስታት ከልማት አጋሮች ጋር በሴኔጋል ተሰብስበው የአፍሪካን የምግብ ምርት አቅም ለመሳደግና አህጉሪቱን የዳቦ ቅርጫት ለማድረግ ስትራቴጂካዊ እቅድ አውጥተናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ከፈረንጆቹ ጥር 25 ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆየውን የዳካር ሁለተኛው የምግብ ጉባዔን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን ጋር በመሆን እንደሚያስተናግዱ ተገልጿል።

የአፍሪካን መመገብ ፤ የምግብ ሉዓላዊነት እና ፅናት የሚል መሪ ሃሳብ አለው የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ።

በአፍሪካ የአመጋገብና ደህንነት መሻሻል፣ የአህጉሪቱን ግዙፍ የግብርና ኃብቶች በመጠቀም ዓለም አቀፍ ንግድን በማሳደግ፣ የገበያ ድርሻን በማስፋት እና በማምረት እና በማቀነባበር እሴት መጨመር ዓላማው እንደሆነም ነው የተገለጸው።

በዓለም በምግብ እጥረት ከሚኖሩ 850 ሚሊየን ህዝብ ውስጥ አንድ ሦስተኛው በአፍሪካ እንደሚገኝ ይገለጻል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አኪንዉሚ አዴሲና ፥ ጉባኤው የፖለቲካ ቁርጠኝነትን፣ የልማት አጋርን እና የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ያንቀሳቅሳል ፤ በጣም አስፈላጊ ፖሊሲዎችን ያዘጋጃል ፤ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያግዛልም ብለዋል፡፡

ይህም ለአህጉሪቱ የምግብ ሉዓላዊነት እና ጽናት የለውጥ ምዕራፍ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የግብርና እድገትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከፍተኛ 5 የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ የአፍሪካን መመገብ ስትራቴጂ ነው፡፡

የአፍሪካ ሀገራት አስከፊ ድህነትን፣ የምግብ እጥረትንም ሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለማስወገድ የተነደፉትን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን ያሳያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.