Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴው እየተነቃቃ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮቪድ-19 እና በግጭት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ባለፉት ወራት መነቃቃት ማሳየቱን የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አሕመድ አብዱልቃድር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ቱሪዝም ሰላምን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ከ2012 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም መጨረሻ የጎብኚ ፍሰቱ ተቀዛቅዞ ነበር።

በተለይም ባለፈው ዓመት በጣም ዝቅተኛ የነበረው የቱሪስቶች ፍሰት በተጠናቀቀው ስድስት ወር ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል ነው ያሉት።

ለአብነትም በ2014 ዓ.ም ወደ ክልሉ 48 የውጭ ሀገር ጎብኚዎች መምጣታቸውን አስታውሰዋል። ይህም በ2011/12 ከነበረው 11ሺህ 700 የቱሪስት ፍሰት አንፃር የነበረው ግጭት ቱሪዝሙን ምን ያህል እንደጎዳው ያሳያል ይላሉ።

በተያዘው በጀት ዓመት የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደነበረበትና ከዚያም በላይ እንዲያድግ እየተከናወኑ ባሉ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች÷ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 82 ሺህ የሀገር ውስጥ እና 662 የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ መስኅቦችን ጎብኝተዋል፡፡

የጉብኝቱ መዳረሻዎችም በዋናነት ዳሎል፣ ኤርታሌ፣ አፍዴራ ሐይቅ እና አላሎ ባድ ፈል መሆናቸውን  ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ከቱሪዝም ዘርፍ የተገኘ ገቢን በተመለከተም በ2014 ዓ.ም ወደ አፋር ከመጡ 48 የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች 33 ሺህ 600 ብር መገኘቱን ጠቁመው÷  ባለፉት ስድስት ወራት ግን ከ662 የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች 662 ሺህ ብር መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡

የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜም በአማካይ አራት ቀን መሆኑን ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡

በአጠቃላይ በአፋር ክልል ያለው የቱሪዝም እንቅስቃሴና የጎብኚ ፍሰት ካለፉት ዓመታት አንጻር መነቃቃት ማሳየቱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ጥር መጀመሪያ ላይ ናሽናል ጂኦግራፊ ብሪታኒያ በአፋር ውስጥ ዳሎልን አካሎ የሚገኘው የደናክል አካባቢ በቀዳሚነት የቱሪስቶችን ቀልብ ይገዛል ሲል በዲጂታል ዕትሙ አስነብቧል፡፡

የደናክል አካባቢ የምድራችን ደረቁ፣ እጅግ ሞቃታማው እና ረባዳማው አካባቢ እንደመሆኑ ፈተና እና ጀብዱ የሚወዱ ጎብኚዎች ሳይጎበኙት እንዳያልፉም መክሯል፡፡

አካባቢው በውስጡ ጨዋማ ወንዞችን፣ ቢጫ ቀለም ያላቸው አሲዳማ እና እንፋሎታማ ምንጮችን እንደ ጅረት የሚፈሱ እሳተ ገሞራዎችን እንደያዘም ጠቅሷል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.