Fana: At a Speed of Life!

አቶ አህመድ ሽዴ ከዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዴንማርክ የልማት ትብብርና ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሚኒስትር ዳን ጀርገንስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብር እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሽዴ÷ከሰላም ስምምቱ በኋላ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ስላሉ ሁለንተናዊ የልማት እንቅሰቃሴዎች፣ በመልሶ ማቋቋሙ ስለተከናወኑ ተግባራት እና ስለሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ዴንማርክ የኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት አጋር መሆኗን የጠቆሙት ሚኒስትሩ÷ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማትና ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ዳን ጀርገንስ በበኩላቸው÷ በቅርቡ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አንስተዋል፡፡

ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማት ድጋፍ፣ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የዴንማርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማስረዳታቸውንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.