Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ነገ የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ያካሂዳል።

በስብሰባውም÷የምክር ቤቱን 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባዔ እና የሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡

ተጨማሪም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለሁለተኛው ምዕራፍ የዘላቂ መሬት አያያዝ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል፡፡

እንዲሁም የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት እና በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መንግስት መካከል የተደረገውን የአሳልፎ መስጠት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች ደንብን፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች አስተዳደር ደንብን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.