Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የ2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ከውጭ ለመሣብ ዐቅዳ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሬት ባንክ እና የልማት ኮርፖሬሽን የ2 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ከውጭ ለመሳብ ዐቅዶ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡

ኮርፖሬሽኑ “ኢንቨስት ኦሪጅንስ 2023” በሚል መሪ ቃል ጥር 18 እና 19 ቀን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ለማስተናገድ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሌንሳ መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ፥ በተጠቀሱት ቀናት የውጭ ባለሐብቶች በዋናነት በተለዩ አምሥት የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራል፡፡

አሁን ላይም ኮርፖሬሽኑ ባለሃብቶችን የሚስቡና ዘላቂ የቢዝነስ አጋርነትን የሚፈጥሩ የቤት ልማት፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የመስተንግዶ እና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎችን በመለየት ቅድሚያ መስጠቱን አስረድተዋል።

ፎረሙ የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ያለመ መሆኑን በመጥቀስም፥ ለዚህም ከሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የንግድ ማኅበረሰብ አጋር አካላት ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችል ምኅዳር ይመቻቻል ነው ያሉት፡፡

ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና የምታደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ እና የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ዓላማ ሰንቆ መነሳቱንም ነው የገለጹት።

ከሀገር ውስጥ ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የተለያዩ የኢፌዴሪ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የኮርፖሬሽኑን ዓላማ በመደገፍ ከፊት የተሰለፉ አጋር አካላት ሲሆኑ ፣ ከግሉ ዘርፍ ደግሞ በግንባታ ላይ የተሠማራው “ኦቪ ግሩፕ” ፣ “ሳልቫቶር” ፣ “ጊፍት ሪል እስቴት” እና የተለያዩ አማካሪ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡

የተፈጠረው መድረክ በኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ፅንሰ-ሐሳቦች እንዲያብቡ እና ሐሳቦቹም እንዲተገበሩ ምቹ ምኅዳር እንደሚፈጥርም አንስተዋል።

በተጨማሪም ፈጠራዎችን እና አዳዲስ የአስተሳሰብ አድማሶችን ለማፍለቅ የሚያስችል ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል ብለዋል።

ከነገ በስተያ በሚካሄደው “ኢንቨስት ኦሪጅንስ 2023” ዓለምአቀፍ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ለመሳተፍ ከዱባይ፣ባህሬይን፣ቱኒዝያ፣ሱዳን እና ኬንያ የመጡ ባለሐብቶች እና ዓለም አቀፍ አጋር አካላት አዲስ አበባ መግባታቸውንም ሌንሳ መኮንን ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.