Fana: At a Speed of Life!

የተያዘን 8 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ በተከሰሰ ግለሰብ ላይ ምስክር ተሰማ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀድሞው የአቪየሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ የክፍል ዋና ኃላፊ አቶ ደረጄ መንግስቱ 8 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ በቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ ላይ ምስክር ተሰማ።

አቶ ደረጄ መንግስቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመንገደኛ የተያዘ 8 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅን ለግል ጥቅሙ አውሏል ተብሎ በቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ ላይ የዐቃቤ ህግ አራት ምስክሮች ተሰምቷል።

የምስክሮችን ቃል ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ 96 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ ከአንድ መንገደኛ ላይ በአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ባለሙያዎች መያዙ የሚታወስ ነው፡፡

ከተያዘ በኋላም ተከሳሹ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥርና ፀረ ፈንጅ መምሪያ ዕፁን ሲያስረክብ ከ96 ኪሎ ግራም ዕፅ ላይ 8 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን ቀንሶ ለግል ጥቅሙ አውሏል በሚል ህዳር 12 ቀን 2015 ዓ.ም ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ነበር።

ተከሳሹ ክሱ ከደረሰውና በችሎት በንባብ ከተሰማ በኋላ ክሱ እንዲሻሻልለት በጽሁፍ አቅርቦ የነበር ሲሆን ፍርድ ቤቱም የተከሳሹን የክስ መቃወሚያ ጥያቄና እና ዐቃቤ ህግ ክሱ ሊሻሻል አይገባም ሲል ያቀረበውን መልስ መርምሮ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ክሱን ለማሻሻል የሚያስችል የህግ መሰረት ያለው ጥያቄ አይደለም ሲል ውድቅ አድርጎታል።

የክስ መቃወሚያው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ተከሳሹ ወንጀሉን አልፈጸምኩም በማለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሰጥቷል።

በተጨማሪም በዛሬው የችሎት ቀጠሮ ዐቃቤ ህግ አራት የሙያ ምስክሮችን አስቀርቦ በወንጀሉ አፈጻጸም ዙሪያ የምስክርት ቃላቸው እንዲሰማ ያደረገ ሲሆን ምስክሮችን ቃል ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለየካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.