Fana: At a Speed of Life!

ባለ 3 መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤትን በሀሰተኛ ሰነድ በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሸጠዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 16 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለ 3 መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤትን የቤቱ ህጋዊ ባለቤት ሳይሰማ በሀሰተኛ ሰነድ በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ሸጠዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ።

በተመሳሳይ ስም በወጣ ሀሰተኛ መታወቂያና ሰነድ ቤቱን የእኛ ነው በማለት የቤቱ ባለቤት ሳይሰማ በመሸጥ ገንዘቡን ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ አምስት ግለሰቦች ናቸው ክስ የተመሰረተባቸው።

ተከሳሾቹ 1ኛ ጳውሎስ ገለጠው፣ 2ኛ ዳዊት ግርማ፣ 3ኛ ፋሲል እሸቱ፣ 4ኛ ከፋለ አለሙ እና 5ኛ ተከሳሽ ዳዊት ግዛው ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ አራት ተደራራቢ የወንጀል ክስ ዛሬ መስርቶባቸዋል።

በዚህ በተመሰረተ ክስ አንደኛ እና ሁለተኛው ክስ በ1ኛ ተከሳሽ ጳውሎስ ገለጠው ላይ ብቻ ቀርቧል።

በዚህ ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ 1 ሀ፣ 2 እና 3 ላይ የተደነገገውን ድንጋጌን በመተላለፍ እንዲሁም የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004 አንቀጽ 66/1 በመተላለፍ፤ በተመሳሳይ ስም በተዘጋጀ ሀሰተኛ መታወቂያ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም በብድር ውል በኮዬ ፈጬ ሳይት በሚገኝ ባለ 3 መኝታ ቤትን የእኔ ነው በማለት የቤቱ ህጋዊ ባለቤት ሳይሰማና ሳያውቅ ቤቱን ሸጧል ተብሎ የቀረበ ነው።

3ኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ እና በ2ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በዚህም 1ኛ ተከሳሽ የእኔ ቤት ነው ብሎ በብድር ውል በህገ ወጥ መንገድ የቤቱ ህጋዊ ባለቤት ሳያውቅ የሰውን ቤት በ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በሸጠበት ወቅት 2ኛ ተከሳሽ ለቤቱ ገዢ 1ኛ ተከሳሽ የቤቱ ባለቤት ነው ብሎ በሀሰት አሻሽጧል ሲል ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ዘርዝሯል።

4ኛ ክስ ላይ ደግሞ በአምስቱም ተከሳሶች ላይ የቀረበ ሲሆን አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች ከሸጡት ገንዘብ ውስጥ 2 ሚሊየን 430 ሺህ ብር ግብረ አበር ናቸው የተባሉት ከ2ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ገንዘቡን በተለያየ መጠን በባንክ ሂሳባቸው በማዘዋወር ለግል ጥቅማቸው አውለውታል ሲል ዐቃቤ ህግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን የችሎት ዳኞች ተሟልተው ክሱን በንባብ ለማሰማት ለነገ በይደር ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.