Fana: At a Speed of Life!

በሀረሪ ክልል ከ799 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀረሪ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ799 ሚሊየን 608 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን እንደተናገሩት÷ በክልሉ በ2015 ዓ.ም በስድስት ወራት 774 ሚሊየን 273 ሺህ 487 ብር ለመሰብስብ ታቅዶ 799 ሚሊየን 608 ሺህ 131 ብር ተሰብስቧል፡፡

በዚህም የእቅዱን 103 ነጥብ 3 በመቶ ማሳካት መቻሉንና የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ25 ሚሊየን 334 ሺህ 643 ብር ጭማሪ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

ገቢውም ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ፣ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤን ለማጎልበት በትኩረት መሰራቱ፤ ከደረሰኝ አቆራረጥ ጋር ተያይዞ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግና የህግ ማስከበር ሥራ በመሠራቱና በተቋሙ የአገልጋይነት ስሜት እንዲጎለብት አሰራር ስርአቶችን የማዘመም ስራ መሰራቱ በገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ አስተዋፅዖ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡

በቀጣይም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በማጠናከር በበጀት አመት ለመሰብሰብ የታቀደው1 ነጥብ 36 ቢልየን ብር ገቢ ማሳካት ይሰራል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.