Fana: At a Speed of Life!

የሞሮኮ አምባሳደር በዓለም ዋንጫው ኢትዮጵያውያን ላሳዩት ድጋፍ አመሰገኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ነዚሃ ሞሐመድ በኳታሩ 22ኛው የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያውያን ላሳዩት ድጋፍ ምስጋና አቀረቡ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በኢትዮጵያ ከሞሮኮ አምባሳደር ነዚሃ ሞሐመድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይታቸውም አምባሳደሯ ኢትዮጵያውያን በኳታሩ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ  ላይ ለሞሮኮ ለገለፁት መልካም ምኞት እና በውድድሩ ወቅት ላሳዩት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሠሩ የገለጹት አምባሳደሯ÷ ኢትዮጵያና ሞሮኮን የሚያገናኙ ብዙ ታሪካዊና ባህላዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ቀጀላ መርዳሳ ሞሮኮን እንዲጎበኙ አምባሳደሯ ግብዣ አቅርበዋል፡፡

አቶ ቀጀላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ለማጠናከር በሞሮኮ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋች ማሰልጠኛ ማዕከል በኩል እገዛ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከአምባሳደሯ ጋር መምከራቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በተለይም በሴቶች አትሌቲክስ ዘርፍ ልምድ መለዋወጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.