Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ወሳኝ ኩነት በሕገ-ወጥ ተግባራት ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮች ተጠያቂ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮችን በሕግና በአስተዳደራዊ እርምጃ ተጠያቂ ማድረጉን አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮናስ ዓለማየሁ እንደገለጹት÷ ባለፉት ስድስት ወራት ከወሳኝ ኩነት አገልግሎት ጋር በተገናኘ በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሳትፈው የተገኙ 57 አመራሮች በሕጋዊና አስተዳደራዊ አሰራር ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ አራት ደላሎችና 32 ተገልጋዮችም በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓልም ነው ያሉት።

በሕግ ተጠያቂ የሆኑት ተገልጋዮች በሕገ-ወጥ መንገድና በሐሰተኛ ሰነዶች ለመገልገል የሞከሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የነዋሪነት መታወቂያ በማመሳሰል በሕገ-ወጥ መንገድ ማተምን ጨምሮ በዚሁ ሥራ በጥቅም የተሳሰሩ ሙያተኞችንና ደላሎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል።

የወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ ሆነው በተገኙት አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ጨምሮ ከኃላፊነት ማንሳትና ከምደባ ውጭ የተደረጉ መኖራቸውንም አብራርተዋል።

ለአብነትም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የወሳኝ ኩነት ጽኅፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት በሕግ ተጠያቂ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በወቅቱ የነበሩት ኃላፊ በሕገ-ወጥ መንገድ ለውጭ ሀገር ዜጋ የጋብቻ ሰርተፊኬት ሲሰጡ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የወሳኝ ኩነት ጽኅፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት በተመሳሳይ ወንጀል በሕግና አስተዳደር ተጠያቂ ተደርገዋል ነው ያሉት።

የወሳኝ ኩነት አገልግሎት በቅሬታና በመልካም አስተዳደር ችግር ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው÷ የአሰራር ማሻሻያው እንዳለ ሆኖ የሕግና የአሰራር ተጠያቂነቱ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኤጀንሲውን አገልግሎት አሰጣጥ በሚመለከት ቅር የተሰኙ ነዋሪዎች በቀጥታ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ማንኛውም ተገልጋይ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ ተግባር ሲመለከት በ 75 33 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ማሳሰባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.