Fana: At a Speed of Life!

ለአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ግምገማ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በየካቲት ወር ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ እየተደረጉ ያሉ የዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ግምገማ ተካሄደ፡፡

36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 42ኛው የህብረቱ አስፈፃሚዎች ጉባኤ በፈረንጆቹ ከየካቲት 15 እስከ 19 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ 30 ተቋማትን በአባልነት የያዘ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል ተብሏል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን÷ ጉባኤው ኢትዮጵያ ከነበረችበት ፈታኝ ሁኔታ እየወጣች ባለችበት ወቅት የሚካሄድ እንደመሆኑ አዎንታዊ ገፅታ ለመገንባት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የህብረቱን ጉባኤ አምና ውጤታማ በሆነ መልኩ ማካሄድ መቻሉን ያስታወሱት አቶ ደመቀ የነበሩ ጉድለቶችን በማሻሻል በተሻለ ስኬት ዘንድሮ ማስተናገድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ለስኬቱም ባለድርሻ ተቋማት በተናበበ መልኩ ቅንጅትን በመፍጠር እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

ብሄራዊ ኮሚቴው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት የእስካሁን የዝግጅት ስራዎችን በዛሬው እለት ገምግሟል።

በግምገማው ላይ እንደተገለፀው ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች በባለድርሻ ተቋማት እየተከናወኑ መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.