Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ  መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 3 ነጥብ 5ሚሊየን ወገኖች ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ የሎጅስቲክ ምላሽና መልሶ መቋቋም ገለጸ።

በኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ የሎጅስቲክ ምላሽና መልሶ መቋቋም ዳይሬክተር ደበላ ኢታና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ደረጃው የተለያየ ቢሆንም በክልሉ በአሥር አርብቶ አደር ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 79 ወረዳዎች ድርቅ አለ።

በድርቁ ምክንያት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ወገኖች ለችግር መጋለጣቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ በአጋር አካላት እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኩል ድጋፍ እየቀረበ ነው ብለዋል።

በድርቁ ምክንያት በሰው ላይ የተመዘገበ ሞት አለመኖሩን በአጽንኦት ገልፀዋል።

በአንጻሩ ከሐምሌ 2015 ዓ. ም በፊት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን፣ ከሐምሌ ወዲህ ደግሞ 184 ሺህ እንስሳት መሞታቸውን ነው አቶ ደበላ የተናገሩት።

በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቀነስም የውኃ እና ሣር (መኖ) እጥረት እንደፈተናቸው ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

126 ሺህ ቦቴዎች የውኃ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ አስፈላጊ ቢሆኑም አሁን ላይ በ70 ቦቴዎች ብቻ ነው ለአስሩም ዞኖች እየቀረበ ያለው ብለዋል።

ለእንስሳት ምግብነት የሚውል ሣር (መኖ) አቅርቦትን በተመለከተም፥ ቢያንስ ለ579 ሺህ እንስሳት ለማቅረብ ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዚህም ጉዳቱ ያየለባቸውን አካባቢዎች መሰረት በማድረግ ወደ ቦረና፣ ምዕራብ ጉጂ እና ምሥራቅ ባሌ ሣር እየተጫነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዝናብ እጥረት ምክንያት በምሥራቅ ባሌ በተከሰተው ድርቅ የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 406 ሺህ ወገኖች በወርልድ ቪዥን አማካኝነት ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ እየቀረበ ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ለሚኖሩ 400 ሺህ ወገኖች ድጋፉ እየቀረበ መሆኑም ተመልክቷል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞንም በ10 ወረዳዎች የሚገኙ 320 ሺህ ሰዎች ለድርቅ በመጋለጣቸው በኬር ኢትዮጵያ በኩል ድጋፉ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

በአርሲ እና ምዕራብ አርሲም በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ድርቅ መኖሩን አቶ ደበላ ኢታና ተናግረዋል።

በዚህም በምዕራብ አርሲ ሻላ እና ሲራሮ አካባቢ ያሉ ወረዳዎች እንዲሁም አርሲ አካባቢ ደግሞ ጎሎልቻ እና ሴሮ አካባቢ ድርቅ መኖሩን ነው ያስታወቁት።

በዮሐንስ ደርበው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.