Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን ሕዝቦች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የጀመሩትን የፖለቲካ ሂደት በስኬት ለመምራት ያላቸውን ጥበብ እና ብቃት አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም በተጀመረው የውይይት ሂደት ላይ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን አጋርነት መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

መሪዎቹ የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነትን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሏቸውን ነጥቦች አንስተው ተወያይተዋል።

በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ሀገራቱ ሊተባበሩባቸው በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ተነጋግረዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው በመጠቆም፥ ኢትዮጵያ ይህ ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል።

የሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለጉብኝት ወደ ሀገሪቱ በመምጣታቸው ያላቸውን አድናቆት በመግለፅ አመስግነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ሱዳን ማምራታቸው ይታወቃል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.