Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱዳን የነበራቸውን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው በሱዳን የነበራቸውን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሥራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ሱዳን ካርቱም ማቅናታቸው ይታወቃል፡፡

በሀገሪቱ በነበራቸው ቆይታ ከሱዳን የሽግግር ሉዓላዊነት ምክር ቤት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጀኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን ጋር ባደረጉት ውይይት ፥ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን አጋርነት አንስተዋል፡፡

መሪዎቹ የሁለቱን ወንድማማች ሀገራት ግንኙነትን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ፣ በቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይም ሀገራቱ ሊተባበሩባቸው በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፥ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው በመጠቆም፥ ኢትዮጵያ ይህ ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት ፍላጎት እንዳላት ነው ያስታወቁት።

የሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሃን በበኩላቸው፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለጉብኝት ወደ ሀገሪቱ በመምጣታቸው ያላቸውን አድናቆት በመግለፅ አመስግነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሱዳን ሪፐብሊክ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተናል ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ጋር ባደረጉት ውይይት የሱዳን ሕዝብ የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት ያላቸውን ዕምቅ ዐቅም እንዲጠቀሙ አበረታተዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን ቆይታቸው በፖለቲካው ሂደት ላይ ከተሰማሩ የተለያዩ የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሦስትዮሽ መፍትሔ አፈላላጊ ቡድን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብ ያልሆነ መርሕ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር የሚሠራ መሆኑንም ነው ያረጋገጡት፡፡

የሱዳን ሕዝብና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን እንዲፈልጉም ማበረታታቸውንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.