Fana: At a Speed of Life!

የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰነድ አልባ ካርታ ዝግጅት ቢሮ ኃላፊ ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ይዞታ አስተዳደር ጽ/ቤት የሰነድ አልባ ካርታ ዝግጅት ቢሮ ኃላፊ አቶ በሀይሉ አባተ ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

ክሱ የተመሰረተባቸው ኃላፊው 638 ካሬ ሜትር የሆነ ይዞታ ለማይገባቸው ግለሰቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታን ያለአግባብ በማዘጋጀት ፈርሞ አፅድቆ በመስጠት ወንጀል ተጠርጥረው ነው።

ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ ያቀረበው የወንጀል ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሹ የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሀ) እና (2) ላይ የተለመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል፡፡

በዚህም ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ስር በሚገኙ 4 የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎችን አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ ያልሆኑ በይዞታው ላይ ቤት ሰርተው የማይኖሩ ግለሰቦችን ቤት ሰርተው የሚያስተዳድሩ በማስመሰል በሀሰተኛ ሰነድ በመመሳጠር 638 ካሬ ሜትር የሆነ በወቅቱ በነበረ አማካይ የሊዝ የጨረታ ዋጋው 2 ሚሊየን 421 ሺህ 288 ብር ከ46 ሳንቲም የሚገመት አራት ይዞታዎች ላይ በማዘጋጀት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎች ፈርሞ በማፅደቅ እንዲሰጥ በማድረግ ነው የተከሰሱት።

ተከሳሹ በዛሬው ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን ፥ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ከጠበቃ ጋር ተማክሮ እንዲቀርብ ለጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.