Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በዓመት በአማካይ እስከ 3 ሺህ የሥጋ ደዌ ታማሚ ይመዘገባል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ከ2 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ የሥጋ ደዌ ታማሚ እንደሚመዘገብ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከቦታ ቦታ የስርጭት መጠኑ ቢለያይም በኢትዮጵያ የሥጋ ደዌ ሕመም መኖሩን በጤና ሚኒስቴር የቲቢ፣ የሥጋ ደዌ እና ሌሎች የሣንባ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

በዚህም በ326 ወረዳዎች ዝቅተኛ፣ በ121 ወረዳዎች መካከለኛ እና በ93 ወረዳዎች ደግሞ ከፍተኛ የሥጋ ደዌ ስርጭት መኖሩን ገልፀዋል።

በ93 ወረዳዎች ውስጥ ከ10 ሺህ ሰዎች መካከል የሥጋ ደዌ ተጠቂው ከአንድ ሰው በላይ ነው ያሉት ኃላፊው፥ ይህ ስሌት ደግሞ ሕመሙ በኢትዮጵያ የማሕበረሰብ ችግር መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ሕክምናው የሚሰጥባቸውን ተቋማት ለማሳደግ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም 5 ሺህ በሚጠጉ የመንግሥት ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

እንዲሁም አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ፣ ቢ ሲ ዲ ሞ፣ ቦሩ ሜዳ፣ ጋንቦ እና ሻሸመኔ ሪፈራል ሆስፒታሎች ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ የሥጋ ደዌ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የጎንደርና ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ይህን አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

የሥጋ ደዌ ሕመም በወቅቱ ሕክምና ካልተደረገለት የአካል ጉዳት በማድረስ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ስለሚያመጣ ሰዎች በቆዳቸው ላይ ነጣ ነጣ ( ቀላ ቀላ) ያሉ ምልክቶች ሲያጋጥማቸው በጊዜ ምርመራ በማድረግ እና በመታከም የአካል ጉዳትን ለመከላከል የድርሻቸውን እንዲወጡም አቅርበዋል።

ምርመራ እና ሕክምናውም በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት በነፃ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.