Fana: At a Speed of Life!

የእንግሊዝ እና የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ እና የኳታር ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በባንክ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁ፡፡

በትናንትናው ዕለት በይፋ በተከፈተው “ኢንቨስት ኦሪጂንስ 2023” ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት መድረክ ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

መድረኩ ከፍተኛ መጠን ያለው ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመሳብ ማቀዱም ተጠቁሟል።

በመድረኩ ተሳታፊ ለሆኑ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችም÷ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ከኳታር ዶሃ የባህረ ሰላጤው እና የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ የንግድ ተወካይ አቶ ያሲን መሀመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ድርጅታቸው በአቅም ግንባታ፣ በፋይናንስ ኢንቨስትመንት እና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት በኢትዮጵያ ከሚገኝ የግል ባንክ ጋር የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረሙን አስታውቀዋል።

በእንግሊዝ ለንደን የሚገኘው የግሎባል ሺፒንግ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጆን ላዋሳ በበኩላቸው ድርጅታቸው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት አካዳሚ ለማቋቋም እቅድ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የኩባንያቸው እቅድ በፊዚዮቴራፒ ዘርፎች፣ በስልጠና ላይ የስፖርት ቴክኒካል ድጋፍ እና በአውሮፓ የአትሌቲክስ ዕውቀት ዘርፎች ኢንቨስትመንቶችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

የህንድ ባለሃብት የሆኑት አሊም ታኩር በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በሮቦቲክስ ፣ በሳይበር ደህንነት እና በስማርት ትራንስፖርት ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ንግዳቸውን ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ነው የተናገሩት።

በፎረሙ የተሳተፉት ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማድነቅ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በዮናታን ዮሴፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.