Fana: At a Speed of Life!

በከንቲባ አዳነች የተመራ ልዑክ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይቷል፡፡
 
በውይይቱም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ዳያስፖራው በሀገር ቤት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ በሚያስችሉ ዕድሎችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡
 
ከንቲባ አዳነች በኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት አንስቶ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝና በርካታ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች እየተመዘቡ መሆኑን አስርድተዋል፡፡
 
አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ያወሱት ከንቲባዋ÷በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ የተደረገውን ርብርብ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩትን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል፡፡
 
የዳያስፖራ አባላቱ በዕውቀታቸው፣ በሃብታቸው እና በዲፕሎማሲው ግንባር በንቃት በመሰለፍ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ መቻላቸውና አኩሪ ገድል መፈጸማቸውን አውስተዋል፡፡
 
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅድሚያ ትኩረት በተሰጣቸው በቤቶች ግንባታ፣ በቱሪዝም፣ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ፕሮጀክቶችን ቀርጸው ለመሰማራት ለሚመጡ የዳያስፖራ አባላት አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
 
በተመሳሳይ የባህርዳር፣ አዳማ እና ደሴ ከተሞች ከንቲባዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ከተሞቹ ዳያስፖራውን ለማሳተፍ በሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
በከተሞቹ ለመሰማራት የሚቀርቡ የኢንቨስትመንት ጥያዎችን ተቀበሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸው በማረጋገጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ለቀረበላቸው ዝርዝር ገለጻና የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ጥሪ በማመስገን፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ በርካታ የውስጥና የውጭ ጫናዎች በመቋቋም ተጨባጭ ትሩፋቶችን እያስገኘ የሚገኝ መሆኑና ይህም እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡
 
በሀገር ቤት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት አቅም፣ ፍላጎት እና ዝግጁነት ያላቸው መሆኑንና በሥራ እንቅስቃሴያቸው ሂደት የመልካም አስተዳደር እና ብልሹ አሰራር ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግስት እያደረገ ያለውን ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ተሳታፊዎች መጠየቃቸውን በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.